የአረንጓዴ ልማት ግንባታን ለማጠናከር እየተሰራ ነው

64

ግንቦት 12/2011  ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ግንባታን በማጠናከር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 የተያዘውን ግብ ለማሳከት እየሰራ መሆኑን የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የተከናወኑ ያለፉት ዘጠኝ ወራት አፈጻጸም የሚገምግም መድረክ በሃዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

በመድረኩ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የነደፈችው የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ለአፍሪካ ሃገራት ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡

“ሶስት መሰረታዊ ግቦች ያሉት ይሄው ስትራቴጂ የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2030 የተያዘውን ግብ እንዲያሳካ በትኩረት እየተሰራ ነው “ብለዋል፡፡

የተያዘው ግብ የተለጠጠ መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰሩ የካርበን ልቀቱን በማመጣጠን የነበረበት ቦታ የማቆየትና በተለምዶ ከሚለቀው 64 ከመቶ ለመቀነስ ግብ እንደተጣለ አመልክተዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ እንዳሉት እስካሁን የተገኘውን ውጤት መለካት የሚያስችል የቴክኖሎጂ አቅም የመገንባትና በአማካሪ የማስጠናት ስራ እየተከናወነ ነ፤ ይህም ለቀጣዩ የእቅድ ዘመን እንደግብዓት ያገለግላል፡፡

ስነ ምህዳራዊና ምጣኔ ሀብታዊፋይዳ ካለው የደን ሃብት አንጸርም ደንን የሚንከባከቡ አካላትንና በተፋሰሱ የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ክፍያ የሚፈጽሙበትን አሰራር ለመተግባር ህግ እየወጣ ነው፡፡

ሁሉም ክልሎች በተሳተፉበት በዚሁ መድረክ በአፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች የሚፈቱበት የልምድ ለውውጥ የሚደረግበትና ቀጣይ አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው ተብሏል፡፡

በኦሮሚያ ክልል አካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቦና ያደሳ በበኩላቸውበክልሉ በርካታ ፋብሪካዎች በመኖራቸው አካባቢ ጥበቃን መሰረት ያደረጉ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ አካላትም በአየር ንብረት ለውጡ ላይ ያላቸው ግንዛቤ የተለያየ በመሆኑ ክትትል የማድረግና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ግንዛቤ ተፈጥሮላቸው ከችግራቸው ባልወጡ በዘርፉ የተሰማሩ 22 ፋብሪካዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዳቸውንም አስታውቀዋል፡፡

የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተው የብክለት ማጣሪያና ሌሎች አየር ንብረቱን የማይበክሉ ግንባታዎች እያከናወኑ ነው፡፡

እንደ ክልልም ህግ በማስከበሩ ተግባር ላይ የተጀመረውን ስራ እንደምርጥ ተሞክሮ ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ልምዳቸውን በማካፈል ከሌሎች ክልሎችም ተሞክሮ የሚወስዱበት መድረክ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን አለመረጋጋት ተከትሎ እቅዶች በተገቢው አለመፈጸማቸውን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ክልል የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ቃቀቦ ናቸው፡፡

የደን ልማቱን በየዓመቱ 1 ከመቶ ለማሳደግ የተቀመጠው ግብ ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡

ነባር ደኖች ከመጠበቅ፣ ከመንከባከብና ህጋዊ ሰነድ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንጻር የተከናወነው ስራም እንደምርጥ ተሞክሮ አቅርበዋል፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መድረክ ያለፉትን ዘጠኝ ወራት የዘርፉን አፈጻጸም በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡም ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም