ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቀጥታ ገቢ 17 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቀጥታ ገቢ 17 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል
አዲስ አበባ ግንቦት 13/2011 በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቀጥታ ገቢ 17 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን ገለጸ።
የባለስልጣኑ የህግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳሬክተር አቶ ታምራት ንጉዜ ለኢዜአ እንደተናገሩ በከተማዋ በዘጠኝ ወሩ አጠቃላይ 26 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 25 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ተሰብስቧል።
ገቢው ቀጥተኛና ቀጥታ ካልሆነ እንደዚሁም ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት የተሰበሰበ ሲሆን ቀጥተኛ ገቢ ትልቁን ድርሻ ይዟል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት የትርፍ እና የደሞዝ ግብርን ከመሳሰሉ ቀጥታ ታክስ ዓይነቶች የተሰበሰበው ገቢ 17 ቢሊዮን ብር መሆኑን አቶ ታምራት ገልፀዋል።
ይህም ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው 14 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸ የ2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እድገት አሳይቷል ተብሏል።
አፈጻጸሙም ከባለፈው ዓመት ጋር በንጽጽር የ19 በመቶ እድገት ማሳየቱን ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በዘጠኝ ወሩ ከተሰበሰበው 25 ቢሊዮን ብር ውስጥ 7 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብሩ ከተጨማሪ እሴት ታክስ እና አገልግሎት የተሰበሰበ ቀጥታ ያልሆነ ገቢ ሲሆን ቀሪውን ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የተገኘ ነው።
ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ ባለፈው ዓመት ከነበረው የአንድ ቢሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል ተብሏል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት አጠቃላይ የተሰበሰበው ገቢ ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እድገት እንዳለውም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የግብር ከፋዩ ገቢን የማሳወቅ ሁኔታ የተሻለ መሆንንና የቁጥጥር ሥራው መጠናከርን ጨምሮ የተለያዩ ሌሎች ተግባራት የግብር አሰባሰቡ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው ካደረጉት ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ገልፀዋል።
አዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ ከ40 እስከ 60 ቢሊዮን ብር ገቢ የማመንጨት አቅም እንዳለው ጥናቶች ያመለክታሉ።
ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ይህ መጠን ገቢ እየተሰበሰበ አይደለም።
ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች ደግሞ በገቢ አሰባሰብ ስርአቱ ገቢን መደበቅ፣ ያለደረሰኝ ግብይትና ሌሎች ይጠቀሳሉ።
ሁኔታውን ለመለወጥ የማስተማግንዛቤ የመፍጠርንና የቁጥጥር ስራን ጨምሮ መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑም ይስተዋላል።