”በትውልዶች ቅብብሎሽ ዘመናት የተሻገረውን የአማራና ቅማንት ህዝቦች የአብሮነት እሴት ማስቀጠል ይገባል”-አክቲቪስት ታማኝ

553

ጎንደር ግንቦት 12 / 2011በትውልዶች ቅብብሎሽ ዘመናት የተሻገረውን የአማራና ቅማንት ህዝቦች የአብሮነት እሴት ማስቀጠል እንደሚገባ አክቲቪስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ጠየቀ፡፡

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን ግሎባል አሊያንስ/ አባላት በማእከላዊ ጎንደር ዞን በግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ወገኖችን ትናንት ጎብኝቷል፡፡

ለዘመናት አብረው የኖሩት ሕዝቦች በጊዚያዊ ግጭት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው እርዳታ ጠባቂ መሆናቸው ልብይሰብራል ብሏል፡፡

የትብብሩ ፕሬዚዳንትአክቲቪስት ታማኝ በየነ በዚሁ ወቅት እንደተናገረው ህዝቡ ለዘመናት ያቆያቸውን እሴቶችን መጠበቅና የአባቶቹን ፈለግ መከተል አለበት።

”እኛ ኢትዮጵያውያን በውጪ ሀገር ስንኖር አብሮን ካልተወለደው፤ ከጥቁሩም ከነጩም ተስማምተንና ሕግ አክብረን ሆኖ ሳለ፤ እንዴት በአገራችን ዜጋችን ከሆነው በደም ከተሳሰረ ወገናችን ጋር በጋራ መኖር ያቅተናል”ሲልም ተናግሯል፡፡

ሁለቱ ህዝቦች አብረው የኖሩ የተዋለዱ ባህልና ቋንቋቸው ጭምር የሚያስተሳስራቸውመሆኑን ገልጾ፣ ”በተፈጠረው ግጭት ጥፋት እንጂ ልማት አልመጣም” ብሏል፡፡

ወደ ቀደመ አብሮነታችሁ ፍቅራችሁ ህብረታችሁና ህይወታችሁ ተመልሳችሁ ማየት በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን ምኞት በመሆኑ ባለን አቅም ሁሉ ለመደገፍም ሆነ ለማቋቋም ጥረታችን ይቀጥላል በማለትም አክቲቪስት ታማኝ ተናግሯል፡፡

ከቡድኑ አባላት ጋር ከአሜሪካ(ቺካጎ) የመጡት የማህበራዊ ድርጅት ትብብር ተቋም ሊቀመንበር አቶ በትሩ ገብረእግዚአብሄር ተፈናቃዮች በአጭር ጊዜ ወደ ቄያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ማህበሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

”ፍቅርና አብሮነትን በማጠናከር ለልጆቻችሁ አብሮ የመኖርን ዘዴ ማውረስ አለባችሁ” በማለትም ምክራቸውን ሰጥተዋል።

የምእራብ ደንቢያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብባቸው ባየ አርቲስትና የሰብዓዊ መብት ተሟጓቹ ታማኝና የስራ ባልደረቦቹ የተፈናቃዮችን ሁኔታ ለመመልከት መምጣታቸው በህዝቡና በአመራሩ ዘንድ ደስታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

በወረዳው በግጭቱ የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም እየተደረገባለው ጥረት በአሁኑ ወቅት 418 መኖሪያ ቤቶች ግንባታቸው መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡

በትክል ድንጋይ ከተማ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩት አቶ ማለደ ገበያ ቡድኑ ተፈናቃዮችን በአካል ለማየት መምጣታቸው ለወገኖቻቸው ያላቸውን ክብር ያሳያል ብለዋል፡፡


በቡድኑ ለተደረገላቸው ድጋፍ  በማመስገን ”ታማኝ ለእውነት የቆመ፤ ለህዝቦቹ ነጻነትና እኩልነት የታገለ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመሆኑ ኩራትም ደስታም ይሰማኛል” በማለት አድናቆቱን የገለጸው በትክል ድንጋይ መጠለያ ጣቢያ የሚገኘው ጋሻው ዋኘው ነው፡፡

ቡድኑ በምእራብ ደንቢያ ወረዳ ጉንትር ቀበሌ ቤት ተሰርቶላቸው ወደ ቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮችን በአካል ለማየት ያደረገው ሙከራ በአካባቢው በጣለው ከባድ ዝናብ ሳቢያ ተስተጓጉሏል፡፡

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን /ግሎባል አሊያንስ/ ለአማራና ለጌዴኦ ዞኖች ተፈናቃዮች በቅርቡ ከ37 ሚሊዮን ብር በላይ መለገሱ ይታወሳል፡፡