ምክንያታዊ ያልሆነ የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ጭማሪ በህብረተሰቡ ላይ አላስፈላጊ ጫና ፈጥ­ሯል - የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ

94

ግንቦት 11/2011 በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ በህብረተሰቡ ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዲከሰት ማድረጉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገልጿል፡፡  

የአዲስ አበባ  አትክልት እና ፍራፍሬ ነጋዴዎች በበኩላቸው የዋጋ ጭማሪው ምክንያት የምርት አቅርቦት እጥረት  ነው ይላሉ፡፡

ከፋሲካ በዓል ጋር  ተያይዞ በአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ላይ የተከሰተው የዋጋ  ጭማሪ ከበዓል በኋላም መሻሻል እንዳላሳየም አንድ አንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

በቄራ ገበያ ማዕከል የተለያዩ አትክልቶችን  ሲገዙ ያገኘናቸው ወ/ሮ ዘቢዳር ንጉሴ እንዳሉት የሽንኩርትና ድንች የዋጋ ጭማሪ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

’’ከዚህ ቀደም በ10 ብር ስንገዛው የነበረው 1 ኪሎ ሽንኩርት በ22 ብር ለመግዛት ተገደናል’’ የሚሉት ወ/ሮ ዘቢዳር እስከ አሁን በተሻለ ዋጋ ስገዙ የነበረው ድንች እንኳን 1ኪሎ 16 ብር መድረሱን ተናግረዋል፡፡  

በበዓላት የአትክልት እና ፍራፍሬ ዋጋ ጭማሪ የተለመደ ቢሆንም የፋሲካ በዓል ካለፈ በኋላም የዋጋ ቅናሽ አለመታየቱን ይገልጻሉ፡፡  

የከተማዋ ነዋሪ ወ/ሮ ዘኪያ ሃሰን በበኩላቸው የአንድ አንድ አትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ዋጋ መናሩ  ሸማቹን እያስመረረ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

የምርቶቹ  ዋጋ መጨመር ምክንያት ግልፅ አይደለም የሚሉት ወ/ሮ ዘኪያ፤ በገበያ ላይ በበቂ ሁኔታ የሚገኙ አትክልቶችም በውድ ዋጋ እየተሸጡ ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአትክልት ተራ በቂ የሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ድንች እና ሙዝ ምርት ተመልክቼያለሁ ያሉት ወ/ሮ ዘኪያ፤ የመሸጫ ዋጋው ከባለፈው ሳምንት ሲነፃፀር የተወሰነ ቅናሽ ያሳየ ቢሆንም አሁንም ተመጣጣኝ አይደለም ይላሉ፡፡

በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ድህረ ፍቃድ ሬጉላቶሪ ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን በየነ፤ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎችና ግለሰቦች ህዝብ  እንዲማረር እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

ሰሙኑን የተከሰተው የዋጋ ንረት ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለውም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ለዋጋ ንረቱ በነጋዴው ማህበረሰብ እንደ ምክንያት የሚቀርበው  የአቅርቦት እጥረት እና የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ተገቢ እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡

ያልተገባ ጥቅም ማግኘት የሚፈልጉ አካላት የምርት እጥረት እንዳለ በማስመሰል የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ ሸማቹን ማህበረሰብ  ስጋት ውስጥ እየከተቱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአትክልት እና ፍራፍሬ የአቅርቦት እጥረት እንደሌለ  የተናገሩት አቶ ካሳሁን፤ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያን ተከትሎ በትራስፖርት ታሪፍ ላይ የተደረገ ጭማሪ አለመኖሩንም አስረድተዋል፡፡

የሽንኩርት እና ድንች ምርቶች ከፍተኛ እጥረት እንዳለ እና በቢሮው ሃላፊ አስተያየት እንደማይስማሙ የነገሩን ደግሞ ከቪፋት አትክልት እና ፍራፍሬ አክስዮን ማህበር አቶ ጸጋዬ ወልደማርያም ናቸው፡፡

አገር ውስጥ የሚቀርበው የሽንኩርት ምርት አነስተኛ በመሆኑ ማህበራቸው ከሱዳን ጭምር በማስገባት 1 ኪሎ በ12 ብር ከሃምሳ ሳንቲም በጅምላ እያከፋፈለ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ከዚህ ቀደም ከመቂና ዝዋይ ይቀርብ የነበረው የሽንኩርት ምርት  በሚፈለገው ደረጃ እየቀረበ እንዳልሆነ የገለፁት አቶ ፀጋዬ የምርት አቅርቦት እጥረቱ የዋጋ ጭማሪ  እንዲከሰት አድርጓል ብለዋል፡፡

ነጋዴው እና አምራቹ በቀጥታ እየተገናኙ አለመሆኑና በመሐል ደላላዎች  የዋጋ ንረት እያስከተሉ  በመሆኑ የግብይት ስርዓቱ ሊስተካከል እንደሚገባም  ተናግረዋል፡፡

ከሻሸመኔ አከባቢ ተመርቶ ይቀርብ የነበረው የድንች ምርት በመቀነሱ እጥረት እንደተከሰተ የገለጹት የክብር ፍሩት ጠቅላላ አገልግሎት ሃላፊ አቶ ዮናስ አስራት፤ ከድንች፣ ሽኩርትና ካሮት ውጭ የሌሎች አትክልት እና ፍራፍሬ መሸጫ ዋጋ ወደ መደበኛው መሸጫ ዋጋ እየተመለሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አንድ ኪሎ 20 ብር ይሸጥ የነበረው ቲማቲም በአሁኑ  ወቅት 10 ብር አየተሸጠ መሆኑንም ለአብነት አንስተዋል፡፡  

መንግስት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የተናገሩት  አቶ ካሳሁን፤ ከእርምጃው ጎን ለጎን በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት የተለያዩ  ምርቶችን በማቅረብ ገበያን የማረጋጋት ስራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም