መምህራን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

286

ግንቦት 10/2011መምህራን መብታቸውን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን የትምህርት ጥራትን የማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮዽያ መምህራን ማህበር ጥሪ አቀረበ።
በመቀሌ ከተማ “ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በጋራ እንጓዝ” በሚል መሪ ቃል ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ሲምፖዚየም ዛሬ ተጠናቋል።

የትግራይ ክልል መምህራን ማህበር 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው ሲምፖዚየም ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የኢትዮዽያ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ የትምህርት ጥራት እንዲረጋገጥ በየደረጃው ያሉ መምህራን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በመምህራን የሚነሳው የመኖሪያ ቤት ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ በመንግስት በኩል እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ የደመወዝና ጥቅማጥቅም ጥያቄም ደረጃ በደረጃ መልስ እንደሚሰጠው ነው ያመለከቱት።

መምህራን መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑንም ተናግረዋል።

መብትን ከመጠየቅ ጎን ለጎን መምህራን ህዝብና አገር አለኝ የሚል ትውልድ የመቅረፅ ግዴታ እንዳለባቸው ተገንዝበው በተለይ ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ዶክተር ገብረመስቀል ካህሳይ በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ ከ34 ሺህ የሚበልጡ የማህበሩ አባላት “ለኔ ምን ተሰራልኝ ብቻ ሳይሆን እኔ ለአገሬ ምን ሰራሁላት የሚል የጸና አቋም ያለው ዜጋ ለመፍጠር ሊሰሩ ይገባል” ብለዋል።

የመቀሌ መምህራን ማህበር አባል መምህር ወይንሸት አሰፋ በበኩላቸው “ለዓመታት የቆየው የመኖሪያ ቤት ችግራችን በትግራይ ክለል መፍትሄ ማግኘቱ በጥሩ ጎኑ የሚታይ ነው ” ብለዋል።

በሲምፖዚየሙ መምህራን፣ ህዝብና አገርን ከአደጋ ማትረፍ የሚችል ትውልድ ለመቅረጽ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ግንዛቤ መያዛቸውን የገለጹት ደግሞ የዓድዋ ከተማ መምህራን ማህበር ተወካይ መምህር ስዩም ይሳቅ ናቸው።

የትግራይ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ሞላ በበኩላቸው ለሦስት ቀናት በተካሄደው ሲምፖዚየም ከ250 የሚበልጡ ተሳታፊዎች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

 “በመምህራንና ተማሪዎች የተሰሩ የፈጠራ ሥራዎች በማህበራዊ ዘርፍ ያስገኙት ውጤት፣ ለመምህራን የተሰጠ ክብርና ጥቅማጥቅም እንዲሁም የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የመምህራን ሚና “በሚሉት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ከአስር በላይ ጥናታዊ ጽሁፎቹ በመድረኩ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።