በጎባ፣ ፍቼ፣ ሚዛን አማንና ጭሮ ከተሞች የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ

90

ግንቦት 10/2011 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተላለፈውን የጽዳት ዘመቻ ምክንያት በማድረግ በጎባ፣ ፍቼ፣ ሚዛን አማንና ጭሮ ከተሞች የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ።
በከተሞቹየጽዳት ዘመቻው የተካሄደው “አካባቢያችንን ከቆሻሻ፤ ውስጣታችንን ከቂምና ጥላቻ እናጽዳ” በሚል መሪ ቃል ነው፡፡

ዛሬ ማለዳ በጎባ ከተማ በተካሄደው የአካባቢ የጽዳት ዘመቻ ላይ የፌዴራልና ኦሮሚያ ክልል የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና የኦሮሚያ የጸጥታ አካላት እንዲሁም የከተማዋ ነዋሪዎች ሳትፈዋል።

በከተማዋ በጽዳት ዘመቻው የተሳተፉት የሃይማኖት አባቶችም የከተማዋን የሰላም አምባሳደርነት ዳግም ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በጽዳት ሥራው የተሳተፉት የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሃጂ መንግስት የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እያደረገ ያለውን ጥረት ህዝቡ ለመደገፍ እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲያጠናክር ጠይቋል፡፡

በከተመዋ የተካሄደው የፀዳት ዘመቻ ከተመዋን ከቆሻሻ በማጽዳት ለነዎቿ ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ መዕከል እንድትሆን ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ያሉት ደግሞ የጎባ ከተማ አስተዳዳር ከንቲባ አቶ አህመድ ሀጂ ናቸው፡፡

በተመሳሳይ ዜና በፍቼ ከተማ የጽዳት ዘመቻ ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች በበኩላቸው በአካባቢያቸው ፍቅርና አንድነትን የሚያጐለብቱ ተግባራትን አጠናክረው በመቀጠል ለተሻለ ማህበራዊ ግንኙነትና እድገት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በጽዳት ሥራው ላይ የተሳተፉ ወጣቶች ፣ ሴቶችና ሰራተኞች ለኢዜአ እንደገለፁት የአካባቢያቸውን ፅዳት፣ ሰላምና ፀጥታ ለማጠናከር  ከመቼውም ጊዜ ባላይ ተባብረውና ተጋግዘው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል ።

ከፅዳት ሥራው ተሳታፊዎች መካከል የፍቼ ከተማ ቀበሌ 04 ነዋሪ ወጣት ባዩ ከበደ እንዳለው የሚኖርበት ከተማ ፅዱና አረንጓዴ እንዲሆን ከህብረተሰቡ ጋር ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚሰራ ተናግሯል።

በተለይ አካባቢውን ከቆሻሻ ከማፅዳት ባሻገር ወጣቶች ለሃገር እንድነት የሚበጁ ተግባራት እንዲፈጽሙና መልካም ሰነ-ምግባር የተላበሱ እንዲሆኑ የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል።

ሌላው አስተያየት የሰጠው የሁለተኛ ደረጃ መምህር በላይ አምባዬ በበኩሉ ለሰላም፣ ለፍቅርና ለወዳጅነት አስተዋጽኦ ያላቸው ተግባራትን አጠናክሮ ለማከናወን መዘጋጀቱን ተናግሯል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮያዊ ባህል የሆኑትን የመተጋገዝ፣ የመወያየትና ይቅር  የመባባል በጐ ባህላዊ  እሴቶችን የሚያጎለብቱ ሥራዎችን  በትምህርት ቤት ውስጥ እንደሚሰራም አስታውቋል፡፡

“የጽዳት ዘመቻው ፍቼ ከተማን ፅዱ  ከማድረግ ባሻገር በህብረተሰቡ መካከል አንድነት የመፍጠር ዓላማ አለው” ያሉት ደግሞ የፅዳት ዘመቻው አስተባባሪና የከተማው ማዘጋጃ ቤት ተወካይ አቶ ገላን ዱኪ ናቸው።

በዘመቻው የከተማው ዋናና የውስጥ መንገዶች እንዲሁም አደባባዮችን ከማጽዳት ባለፈ በቆሻሻ የተዘጉ ቱቦዎችን የመክፈት ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።

የፍቼ ከተማ አስተዳደርና ነዋሪዎች የመሪዎቹን በጎ ተግባር በእኔነት ስሜት እንደተቀበለ የገለጹት ደግሞ የፍቼ ከተማ ከንቲባ አቶ ሁንዴ ከበደ ናቸው ።

ህብረተሰቡ ለጽዳት ስራው ተባባሪ እንደሆነ ሁሉ ውስጡን ከቂምና ጥላቻ በማጽዳት የተጀመረውን ለውጥ እንዲያጠናክር አስገንዝበዋል።

የሚዛን ከተማ ነዋሪዎችም ሀገር አቀፉን የጽዳት ዘመቻ ጥሪ በመቀበል ዛሬ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የጽዳት ዘመቻ አካሂደዋል።

የጽዳት ዘመቻው ቀጣይነት ላለው አካባቢን የማስዋብ ሥራ መነሳሳት ከመፍጠሩ ባለፈ አንድነትና አብሮነትን እንደሚያጠናክርም የጽዳት ዘመቻው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የጽዳቱ ተሳታፊዎች መካከልም የሕብረት ቀበሌ ነዋሪ አቶ አህመድ መሀመድ “ሁላችንም የአካባቢያችንን ጽዳት በመጠበቅ ከተማችንን ለኑሮ ተስማሚና ለጎብኝዎች ተመራጭ ማድረግ አለብን” ብለዋል፡፡

የሚዛን አማን ከተማ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ችግር ያለበት መሆኑን ጠቁመው ዘመቻው የከተማ ጽዳት በቀጣይ እንዲተኮርበት ያደርጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

እንደሀገር እየተካሄደ ያለውን የጽዳት ዘመቻ ምክንያት በማድረግ በከተመዋ የተጀመረው አካባቢን የማድዳት ተግባር ቀጣይነት ሊኖረው  እንደሚገባአቶ አህመድ ጠቁመዋል፡፡

የአካባቢን ጽዳት በዘመቻ መጀመሩ በነዋሪው ዘንድ ለቀጣይ መሰል ሥራዎች መነሳሳትን እንደሚፈጥር የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ መሰረት ጌታቸው የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡

“ከአካባቢ ጽዳት በተጨማሪም ሁሉም ዜጋ ራሱን ከእኩይ አስተሳሰብ ማራቅና ለሀገር አንድነትና ዕድገት መተባበር ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

በከተማው የቆሻሻ አያያዝና አወገድ እንቅስቃሴው በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው “በእዚህ በኩል ሁሉም ነዋሪ ለከተማው ጽዳትና ውበት በኃላፊነት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

እሳቸውም ከአካባቢያቸው ነዋሪዎች ጋር በመሆንና የጽዳት ሥራቸውን ባማጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ዜና በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የጭሮ ከተማ ነዋሪዎች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የጽዳት ሥራ ያከናወኑ ሲሆን በጽዳት ዘመቻውም የከተማዋ ምክትል ከንቲባና የተለያዩ የህበረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም