አዕምሮን ከጥላቻና ከዘረኝነት በማጽዳት ለአገር አንድነት መቆም ይገባል…በጋምቤላ ከተማ የጽዳት ተሳታፊዎች

202

ግንቦት 10/2011 አዕምሮን ከጥላቻና ከዘረኝነት በማጽዳት ለአገር አንድነት መቆም ይገባል ሲሉ በጋምቤላ ከተማ በሁለተኛው አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

ዛሬ ጧት በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላትና የከተማዋ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል፡፡

በጽዳቱ ከተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት አካባቢን በማጽዳት ጤናን ከሚያውኩ ነገሮች ራስን መጠበቅ እንደሚቻል ሁሉ አዕምሮን ከጥላቻና ከዘረኝነት በማጽዳት ሰላምና አንድነትን ማስጠበቅ ይገባል።

እያንዳንዱ ዜጋ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የአገር አንድነትን በማጠናከር በኩል የድርሻውን መወጣት እንዳለበትም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡

ከጽዳቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኡቦንግ ጋሜ “የግልና የአካባቢ ጽዳት ለጤና ጠንቅ የሆነውን ቆሻሻ ለማስወገድ ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ የህዝብን አንድነት የሚያውኩ ችግሮችን በጋራ ማስወገድና ለዘላቂ ሰላም መስራት  ይገባል” ብለዋል።

በተለይም አዕምሮን የህዝቡን አንድነት ከሚሸረሽሩ ጥላቻ፣ ጎሰኝነትና ዘረኝነት በማጽዳት የህዝቦችን አብሮነት መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ድርሻ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።

“አካባቢን ማጽዳት ከተቻለ ጤናችን ስጋት ውስጥ አይገባም፤ በተመሳሳይ በህዝቡ መካከል ያለው አብሮነት ሲጠናከር ለሰላማችንና ለአንድነታችን ስጋት የሚሆን ነገር አይኖርም ” ያሉት ደግሞ  ሌላው የጽዳት ሥራው ተሳታፊ ወይዘሮ አጁሉ አቻር ናቸው፡፡

በመሆኑም የአካባቢን ጽዳት ከመጠበቅ ባለፈ የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለማጠናከር አዕምሮን ከአክራሪ ብሔርተኝነትና ጠባብነት ማጽዳት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ረዳት ኢንስፔክተር ወልደገብርኤል ተክሉ በበኩላቸው አካባቢን በጋራ ማጽዳት ጤናማ ህብረተሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ከማገዙ በተጨማሪ ህዝቡ ለልማት አንድነቱን እንዲያጠናከር በማድረግ በኩል ፋይዳ እንዳለው ነው የገለጹት፡፡

በተለይም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በዘርና በቀለም ሳይለያዩ በጋራ አንድ ላይ ማጽዳታቸው ህብረትና አንድነታቸውን ለማጠናከር የጎላ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ሀገራዊ አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ሊያግዝ እንደሚገባም አመልክቷል።

“የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ እውን ለማድረግ አካባቢን ከቆሻሻ፤ አዕምሮን ከጥላቻ ማጽዳት ይገባል” ያሉት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ናቸው።

ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በአካባቢው የተጣለን ቆሻሻ በማጽዳትና ጥላቻና ዘረኝነትን በመጠየፍ ለክልሉ ልማትና እድገት ብሎም ለአገር አንድነት መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

በጽዳት ዘመቻው ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች፣ የጸጥታ አካላትና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል ፡፡