የሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን ለመላው አፍሪካ ጨዋታ የማጣሪያ ውድድር ኡጋንዳ ገብተዋል

146

ግንቦት 11/2011 የኢትዮጵያ ሴቶች ቮሊቦል ብሔራዊ ቡድን በኡጋንዳ ለሚካሄደው የዞን 5 የማጣሪያ ጨዋታ ለመሳተፍ ትናንት ማምሻውን በውድድሩ ስፍራ ኢንቴቤ ከተማ ገብተዋል

በዞን 5 የመላው አፍሪካ የማጣሪያ ጨዋታ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄደድ ሲሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ ኡጋንዳ፣ ኬንያና ሩዋንዳ ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ብሩህ ተክለሃይማኖት ለኢዜአ እንደገለጹት 12 ተጫዋቾችን በመያዝ ላለፉት ለ10 ቀናት ለማጣሪያው ውድድር ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል።

12 ተጫዋቾች የተመረጡት ከጌታዘሩ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችና ኢትዮጵያ ውሃ ስራ የቮሊቦል ክለቦች እና ከደቡብ ክልል እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑ አምበል ዮዲት አዲስ ከሲሸልሱ አየስላንድ ዌቭ መመረጣቸውን አመልክተዋል።

የዞን አምስት አባል አገራት የሆኑት ግብጽና ታንዛንያ በመጨረሻው ሰአት ከማጣሪያው ውድድር ራሳቸውን እንዳገለሉ የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ አስታውቋል።

ለሶስት ቀናት በሚካሄደው የመላው አፍሪካ የማጣሪያ ውድድር በድምር ውጤት አጠቃላይ አሸናፊ የሚሆነው በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ በሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታ መሳተፉን አንደሚያረጋግጥም ጠቁመዋል።

ለመላው አፍሪካ ጨዋታ ለመሳተፍ በአፍሪካ ሰባት ዞኖች የማጣሪያ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን በአጠቃላይ በየዞኖቹ አሸናፊ የሚሆኑ ብሔራዊ ቡድኖች በመላው አፍሪካ ጨዋታ ላይ የሚሳተፉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም