ለአገር እድገት የማይበጁ አመለካከቶችን በማስወገድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ

225

ግንቦት 11/2011 ለአገር እድገት የማይበጁ ቆሻሻ አመለካከቶችን በማስወገድ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ የሐረሪ፣ የሶማሌና የአፋር ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ተናገሩ።

ርዕሳነ መስተዳድሮች ይህን የተናገሩት “አካባቢያችንን ከቆሻሻ ውስጣችንን ከቂምና ከጥላቻ እናጽዳ” 
በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በሐረሪ ክልል በተካሄደ የጽዳት ዘመቻ ላይ ነው። 

የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት የጽዳት 
ዘመቻው ዋና ዓላማ የጥላቻ አስተሳሰብን ወደ ጎን በመተው ቆሻሻንና መጥፎ አመለካከትን በማስወገድ አንድነትን መፍጠር ነው። 

በመሆኑም ህብረተሰቡ “እኔ ብቻ” የሚል አመለካከትን ማስወገድና በህዝቦች መካከል 
ቅራኔ ለመፍጠር የሚሯሯጡ አካላትን አንድነቱን በማጠናከርና በማቀራረብ መታገል እንዳለበት አስረድተዋል። 

ለዜጎች መፈናቀል ምክንያት የሆኑ ጥቅም ፈላጊዎችን በማስተማር ከድርጊታቸው 
እንዲቆጠቡ ከማድረግ ባለፈ ጥፋተኞችን ለህግ በማቅረብ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው እንደሚገባም አመልክተዋል።

“መጥፎ የሚባል ግለሰብ የለም፣ መጥፎ የሚባል የሰው አመለካከት ግን 
ይኖራል” ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ አመለካከቶችን ታገሎ ማሸነፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።

“አገራችን ለሁላችንም ትበቃለች እርስ በርስ ተደጋግፈን ለጋራ አንድነትና ለአገራዊ ልማት መስራት አለብንም” ብለዋል። 
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ዑመር በበኩላቸው “ለአገር እድገትና ሰላም የማይበጅ ቆሻሻ አስተሳሰብን በማስወገድ የክልሎችን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ማሳደግ ይገባል” ብለዋል። 

የጽዳት ዘመቻው ቂምና ጥላቻን በማስወገድ በንጹህ ፍቅር ተቻችሎ ለመኖር የሚያስችል መልዕክት ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል።
 ጽዳት ለሰው ልጅ መሰረታዊ ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ናቸው።

“አካባቢ ሲጸዳ ጤናማ ህብረተሰብም ይፈጠራል፤ በእዚህም ደስተኛ ሆኖ መኖር ይቻላል” ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ የጽዳት ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል። 

ቆሻሻን ከማጽዳት ጎን ለጎን እርስ በርስ ሊያጋጭ የሚችል የማይበጅ አመለካከትን በማስወገድ ወደ ተሻለ ደረጃ መድረስ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው “ቆሻሻ አመለካከት ይዞ በጎ ነገር ማሰብ አይቻልም” ብለዋል።

ንጹህ አመለካከትን ማጎልበት ለአገርም ሆነ ለዜጎች ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት ። 

በጽዳት ዘመቻው ከተሳተፉ የከተማው ነዋሪዎች መካከል ወጣት ኤልያስ አህመድ 
የጽዳት ዘመቻው በከተማውም ሆነ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለአንድ ዓላማ ማሰባሰብ ያስቻለ መሆኑን ተናግሯል።

 በሐረሪ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ዛሬ በተካሄደው የጽዳት ዘመቻ
 የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የአፋርና የሶማሌ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ፣ ሌሎች የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ነዋሪዎች ተገኝተዋል።