ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የፅዳት ዘመቻ አከናወኑ

196

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2011ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች ከማለዳው ጀምሮ በአዲስ አበባ የፅዳት ዘመቻ አካሄዱ። 
ዛሬ ከማለዳው 12 ሰአት ከ30 ጀምሮ ጀምሮ በተካሄደው ሁለተኛው አገር አቀፍ የፅዳት ዘመቻ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና ቀዳማዊ እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ የተገኙት ከዚህም ማልደው ነበር።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሊጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያና የተቋሙ ሰራተኞችም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ 

ጋር በመሆን አካባቢውን ሲያጸዱ አርፍደዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ  የጽዳት ዘመቻ የአንድ ወቅት ሳይሆን  በዘላቂነት መከናወን ያለበት ጥሩ የለውጥ ጅማሮ መሆኑን በዚሁ ጊዜ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀድሞው መስሪያ ቤታቸው በመገኘት የጽዳት ዘመቻውን ማካሄዳቸው የሚኒስቴር መስሪያ  ቤቱን ሰራተኞች  ያስደሰተ እንደሆነም ተናግረዋል።

በቀጣይም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በቋሚነት አካባቢውን የማጽዳት ተግባር ለማከናወን ዝግጁ  መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

 የጽዳት ዘመቻው አካባቢን ከማጽዳት ባለፈ ውስጥን የማጽዳት ፋይዳም እንዳለው አንስተዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አካባቢ የተደረገው የጽዳት ዘመቻ በአካቢው የሚኖረው ህብረተሰብ ለጽዳት  የሚያስፈልገውን ቁሳቁስ በማዘጋጀት በትብብር ማፅዳት ችሏል።

በአዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች እንዲሁም የከተማዋ  ነዋሪዎች በፅዳት ዘመቻው ተሳትፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት የመጀመሪያ ዙር አገር አቀፍ የጽዳት ዘመቻ  ሚያዚያ 6 ቀን 2011 ዓ.ም መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የፅዳት መርሀ ግብሩ የቆሸሹ አካባቢዎችን በእጃችን እያፀዳን በጥላቻ፣ በቂም በቀል እና በቁርሾ የቆሸሹ  ጭንቅላቶቻችንን በሰላም፣ በይቅርታ እና በፍቅር ለማፅዳት አዲስ ምዕራፍ የምንከፍትበት ከአካባቢ ፅዳት የዘለለ  ሀገር የመለወጥ እና ህብረተሰብ የመገንባት ዘመን ተሻጋሪ ዓላማ መሆኑ ይነገራል።፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም