በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተቋረጠውን ትምህርት ለማስቀጠል መግባባት ላይ ተደረሰ

61

ግንቦት 11/2011 በተማሪዎች መካከል ግጭት በመፍጠር የመማር ማስተማሩን ሂደት ያስተጓጎሉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፤ ለአንድ ሳምንት የተቋረጠውን ትምህርት ለማስቀጠል ከተማሪዎች ጋር መግባባት ላይ መደረሱም ተመልክቷል።
የዩኒቨርሲቲው ማናጀመንት አባላት የተቋረጠውን ትምህርት ማስቀጠል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከአማራ ክልል ከመጡ ተማሪዎች ጋር ትናንት ተወያይተዋል፡፡ 

በዚሁ ጊዜ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንቱዶክተር ያሬድ ማሞ እንደተናገሩት፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሀገሪቱ የጀመረችውን ሁለንተናዊ ለውጥ ከዳር ለማድረስና ከድህነት የሚያላቅቁ የነገ ተስፋዎችን የማፍራት ኃላፊነት አለባቸው።

ተማሪዎች በብሔር ተለያይተው የሚጋጩበት መሰረት እንደሌለ ተናግረው፣ በመካከላቸው አለመግባባት ሲፈጠር በሰከነ ውይይት የመፍታት ኃላፊነት ሊያዳብሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።

እንደፕሬዚዳንቱ ገለጻ ተማሪዎቹ ለጥቃቅን ችግሮች ቦታ ከመስጠት ይልቅ የመጡበትን የትምህርት ዓላማ ማሳካት ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ሰሞኑን በችግሩ መክንያት በደረሰባቸው መጉላላትና ይቅርታ የጠየቁት ፕሬዚዳንቱ፣ በግጭቱ የተጎዱ ልጆች ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንና እስኪሻላቸው ድረስ ድጋፉ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

“በግጭቱ የተቃቃሩ ተማሪዎችን ከማስታረቅ ጎን ለጎን በተማሪዎች መካከል ሁከትና ግጭት በመፍጠር አንድነታቸውን ለመናድና የመማር ማስተማሩን ተግባራት ያሰናከሉ ተማሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው” ብለዋል፡፡

ተማሪዎች ከአስተዳደር በደል፣ ከአንዳንድ መምህራን አድሎአዊ አሰራር፣ ከደህንነት ስጋት እንዲሁም ከመማር ማስተማር ሂደት ጋር በተያያዘ ያቀረቧቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ዩኒቨርሲቲው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ነው ዶክተር ያሬድ የተናገሩት፡፡

“የዩኒቨሲቲው ከፍተኛ አመራር ፣መምህራንና ሠራተኞች እንደታላቅ ወንድምና እህት ሆነን እንደ ሁልጊዜው ነጻና ገለልተኛ ሆነን ችግራችሁን ለመፍታት እንሰራለን “ ብለዋል፡፡ 

የፌደራል ፖሊስ ሻለቃ አዛዥ ኮማንደር ሞላ አሰፋ በበኩላቸው ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት በተቀናጀ መንገድ የተማሪዎች የደህንነት ስጋት ለመፍታት ሌት ተቀን እንደሚሰሩ ተናግረል፡፡

“ከአምና ጀምሮ በተማሪዎች መካከል ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር አንዱን ከሌላው ለማጋጨት የሞከሩ አጥፊዎችንአጥርተን ጨርሰናል፤ በቀጣይ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ይሰራል” ብለዋል፡፡ 

ተማሪዎች ጥያቄዎቻቸው በአጭርና በረዥም ጊዜ እንደሚፈቱ አምነው የመጡበትን አላማ በማሳካት ሀገርና ራሳቸውን ለመለወጥ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው ኮማንደሩ አያይዘው ገልጸዋል ፡፡

‹‹ከእርስ በርስ ግጭት የሚያተርፍ የለም፣ ውጤቱ ራስንና ሀገርን ለውድቀት መዳረግ ነው፤ ከየመን፣ ከሶርያና ከሊቢያ ልንማርና ሀገራዊ ለውጡን በፍቅርና በህብረት ልናሳድገው ይገባል›› ብለዋል፡፡

እንደኮማንደር ሞላ ገለጻ ከግጭቱ ጀርባ የተለየ አላማ ያነገቡና የሚገፉ አካላትን ተማሪዎች ትኩረት ሊሰጧቸው አይገባም፡፡ 

በውይይቱ ላይ የተካፈሉ ተማሪዎች በበኩላቸው ወደትምህርት ገበታቸው ለመመለስ ፍላጎት ቢኖራቸውም የደህንነት ስጋት እንደሚሰማቸው ገልጸዋል፡፡

የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ በመኖሪያ ሕንጻዎች የተለየ ፍተሸ በማድረግ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡ 

በዩኒቨርሲቲው የ3ተኛ ዓመት ተማሪ ሰለሞን አያሌው “ዓላማችን መማር ቢሆንም በማንነታችንላይ ያነጣጠር ጭቆናና መድሎ ስለበዛብን የሚመለከተው አካል መፍትሄ ይስጠን” ብሏል፡፡ 

ሃሳባቸውን ለመግለጽ ባደረጉት ጥረት ውስጥ ወንጀል ፈጻሚ ከነበረና በማስረጃ ከተረጋገጠ አጋልጠው ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከተማሪዎቹ ተወካዮች መካከል የ5ተኛ ዓመት ተማሪ ሳሙኤል አበራ በአማራና በኦሮሞ ተማሪዎች መካከል መጠነኛ ግጭት ተፈጥሮእንደነበር አስታውሶ፣ ተማሪዎች በደረሰበባቸው የፍትህና የአስተዳደር ችግር ዩኒቨርሲቲውን ለቀው መውጣታቸውን አመልክቷል።

በተደረገው ውይይት ተማሪዎች ወደግቢ ለመመለስ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተናግሮ፣ በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና የፍትህ አካላት የተማሪዎችን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቃል እንደገቡላቸው ገልጸዋል። 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ለኢዜአ እንደተናገሩት ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉና ያነሷቸው ችግሮች እንዲፈቱላቸው በአስተዳደሩ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም