የሀሰት መረጃ ማሰራጨትና ሀሳብን በነጻነት መግለጽ በመቀላቀሉ ለሀገር ደህንነት አሳሳቢ ሆነዋል

110

ግንቦት 11/2011 የማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎችን ትክክለኛነት ለመለየት ግዜ መውሰዱ፤ ሀሰተኛ መረጃና ሀሳብን በነጻነት መግለጽ መቀላቀሉ ለሀገራዊ ደህንነት ስጋት እየሆነ መምጣቱን ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የጋዜጠኝነት መምህር ኤልያስ ወርቁ በኢትዮጵያ የሀሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

የመረጃን ትክክለኛነት ማጣራት የጋዜጠኛ ብቻ አይደለም ያሉት መምህር ኤልያስ፤ የመረጃውን ባለቤትና የቀድሞ ዘገባዎቹን እንዲሁም አዲሱን ዘገባ ከተለያዩ መረጃ ምንጮች ማመሳከር አስገዳጅ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች በፍጥነት መዘዋወራቸው በቀላሉ ለማጣራትና ትክክለኛነታቸውን ለመለየት ጊዜ መውሰዱ ጉዳቱን የከፋ እያደረገው ነው፡፡

የመረጃዎቹን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፤ መረጃውን ማን አሰራጨው፣ ለምን ዓላማ፣ መረጃው ከማን ተሰበሰበ የሚሉና  የህብረተሰቡን የልብ ትርታዎች ለመዳሰስ ያደረገውን ጥረት በትኩረት ማየት የተደራሲያኑ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ የሀሰት ፎቶዎችን  ለመለየት ’’የመጠናቸው ማነስና በጥንቃቄ ለክፋት መሰራታቸው’’ ትክክለኛውን ለመለየት አስቸጋሪ አድርጎታል ያሉት ደግሞ የኮምፒውተር፣ የፎቶና ቪድዮ ባለሙያ አቶ ያሬድ መካሻ ናቸው፡፡ 

በተለይም “የፎቶ ማሳመሪያ ቴክኖሎጂ በፍጥነት እየዘመነ መምጣቱና የኛ ህብረተሰብም ከቴኖሎጂ ጋር ያለው ቁርኝት እምብዛም ካለመሆን ጋር ተደምሮ  የሀሰት መረጃዎችን ጉዳት ጨምሮታል” ነው ያሉት፡፡

“ሀሳብን በነጻ መግለጽና መረጃን በሀላፊነት ማስተላለፍ በሁሉም ሀገራት አከራካሪ ነው” የሚሉት መምህር ኤልያስ፤ የመናገር እድሉ ስለ ተገኘ ብቻ የሰዎችን ደህንነት ስጋት ላይ የሚጥል መረጃን ማስተላለፍ መገደብ አስገዳጅ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡

ሀገራት የሀሰት መረጃዎችን ለመከላከል የህግ፣ የቴክኖሎጂና የግንዛቤ እንዲሁም እነዚህን በማጣመር ጥቅም ላይ እያዋሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ጀርመን፣ ሲሪላንካና ግብጽ የጥላቻ ንግግርን ለመግታት ህግ ተግባራዊ ሲያደርጉ፤ አሜሪካም የአልጎሪዝም ፕሮግራም በመስራት በቴክኖሎጂ መረጃን ለማጣራት እየሰራች ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ ሀሰተኛ መረጃዎች እየተበራከቱ ለህብረተሰቡና ለሀገር ደህንነት ስጋት እየሆኑ በመምጣታቸው መንግስት ችግሩን ለመቆጣጠር ረቂቅ ህግ ማዘጋጀቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

ችግሮቹን ለመቆጣጠር ተቋማትን  በማቋቋም  እንደ “ሲኖብስና ፋክት ቼክ” ከመሳሰሉት  ስልክ ደውለው መረጃዎችን ከምንጩ የሚያረጋግጡበት ስርአት እንዳለም ገልጸዋል፡፡

የኮምፒውተር ባለሙያ አቶ ያሬድ በበኩላቸው ችግሩን በመለየት ራስን ከስህተት ለመቆጠብ ከተለያዩ ሚዲያዎችና የመረጃ ምንጮች በማመሳከር ማየት አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ 

መደበኛ ሚዲያዎች ፈጣን መረጃዎችን ለህብረተሰቡ በማድረስ በሀሰተኛ መረጃ እንዳይታለሉ የበኩላቸውን ማበረክት እንደሚገባቸውም መክረዋል፡፡

የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሰሞኑን በሰጠው መግለጫ ባለፈው አንድ ዓመት የማህበራዊ ሚዲያ ሀሰተኛ ዜናዎች፣ ጽንፈኛ ብሔርተኝነት፣ ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶችና ህገ-ወጥ የጦር መሳርያ ዝውውር ለዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የደህንነት ስጋት ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሷል፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም