ፀረ-ውድድር የግብይት ስርዓትን ለመከላከል ተፅእኖ ፈጣሪ የሸማቾች ማህበራትን ማቋቋም ይገባል ተባለ

76
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2010 በከተሞች አካባቢ እየተባባሰ የመጣውን ውድድር አልባና ህገ-ወጥ ግብይትን ለመከላከል ተጽእኖ ፈጣሪ የሸማቾች ማህበራት መቋቋም እንዳለባቸው የገበያ ጥናት ተመራማሪና መምህር ገለፁ፡፡ የማህበራቱ መኖር በመንግስትና በሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመከላከል የሚደረጉትን ጥረቶች በማጠናከር ለሸማቹ ብሶት ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝም ተናግረዋል። ጥራታቸውን ያልጠበቁና ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶችን ለገበያ ማቅረብ፣ የተጋነነ ዋጋ መጠየቅ፣ ያለምክንያት የዋጋ ጭማሪ ማድረግና በተመሳሳይ ምርቶች ላይ ወጥ የሆነ ዋጋ መተመን ጤናማ ውድድር እንዳይፈጠር እያደረጉ ካሉ ተግዳሮቶች መካከል ይጠቀሳሉ። ከዚህም ሌላ የግብይት ሰንሰለቱ አግባብ ባልሆነ መንገድ መራዘሙም በተለይ ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ለሚታየው ችግር ቁልፍ ምክንያት መሆኑም ተመልክቷል። እነዚህ ችግሮች ለዕድገት የሚጠቅም የገበያ ውድድርን ከመግታት ባሻገር ሸማቹን ለምጣኔ ኃብትና ለጤና ቀውሶች እየዳረጉት መሆኑን ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸው አካላት ለኢዜአ ገልፀዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ስራ ኮሌጅ የገበያ ጥናት ተመራማሪና መምህር ዶክተር ጌቴ አንዱዓለም እንደሚሉት "በአሁኑ ወቅት እነዚህን ችግሮች በመጋፈጥ ጤናማ የግብይት መስተጋብር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ሸማች ማህበረሰብ በኢትዮጵያ የለም"፡፡ በተለይም በሌሎች አገራት ለሸማቹ ማህበረሰብ ቋሚ መረጃዎችን የሚሰጡ፣ ህገ-ወጥ የንግድ አሰራሮችን በማጋለጥ የሚሞግቱ፣ በነጋዴው ማህበረሰብ ላይ ተፅእኖ በመፍጠርና በህግ እየተከራከሩም መብት የሚያስጠብቁ ማህበራት አሉ። በመሆኑም ከሸማቾች ማህበር ጋር በተያያዘ የሌሎች አገራትን ምርጥ ተሞክሮ በመለየትና ከአገሪቱ ሸማች ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ በኢትዮጵያ ገለልተኛ ማህበር የሚቋቋምበትን ምህዳር መፍጠር እንደሚገባ ዶክተር ጌቴ አሳስበዋል። የማህበሩ መኖር በመንግስት በኩል የተጀመሩትን ጥረቶች በማጠናከር የሸማቹን ህዝብ የቆየ ብሶት ለመፍታት ያግዛል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በግብይት ስርዓቱ ውስጥ ሸማቹን ከጉዳት ለመጠበቅ የተቋቋመው የንግድ ተወዳዳሪነትና የሸማቾም ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የአገሪቱ ሸማች ማህበረሰብ መብቱን በወጉ ተገንዝቦ ድምፁን ማሰማት የሚችልበት ቁመና ላይ አይደለም ይላል፡፡ በባለስልጣኑ በትምህርት ስልጠናና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት የትምህርት ባለሙያ አቶ ሰይፉ አየለ እንደሚሉት በአገሪቱ የግብይት መስተጋብር ውስጥ የተንሰራፉትን ህገ-ወጥ አሰራሮች ህግ በማውጣት ብቻ መለወጥ አይቻልም፤ ይልቁንም በእውቀትና በመረጃ የበለፀገ ሸማች ማህበረሰብን መፍጠርን ይሻል፡፡ የኢትዮጵያ የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ዓላማም የዚህ ዓይነት ሸማች ማህበረሰብ እንዲፈጠር  ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው ያሉት ባለሙያው “ሸማቹ ግንዛቤው ጎልብቶ፤ ሞጋችና ጠያቂ እስኪሆንና እስኪደራጅ መንግስት የበኩሉን በማድረግ ለሸማቹ ጥበቃ ያደርጋል፤” ነው ያሉት፡፡ ሸማቹ ገለልተኛ የሆነ ማህበር የማቋቋም መብቱ ህገ-መንግስታዊ ከመሆኑም ባሻገር በመንግስት በኩልም የሚበረታታ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በበኩሉ በአገሪቱ ነጋዴዎች ዘንድ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች እንደሚስተዋሉ አስታውቋል። በምክር ቤቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ አበበ እንደሚሉት ነጋዴው የተጋነነ ዋጋን ከመጠየቅ ጀምሮ ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶችን ለሸማቹ ያቀርባል። የግብይት ችግሩን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ሸማቹ ማህበረሰብ ድምፁን ከፍ አድርጎ ማሰማትና በነጋዴውም ሆነ በመንግስት ላይ ተጽእኖ ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር ለነጋዴውም ፍትሃዊ የገበያ መወዳደሪያ ምህዳር መፍጠርን ማካተት እንዳለበትም አቶ ደበበ ገልጸዋል። በንግድ አሰራርና ተያያዝ ጉዳዮች ዙሪያ ያሉት ህጎች፣ ፖሊሲዎች፣ አሰራሮችና አደረጃጀቶችን ሁሉ ችግሩን ለመፍታት በሚያስችል መንገድ መፈተሽ እንዳለባቸውም አቶ ደበበ ገልፀዋል። ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት በአገሪቱ የንግድ ተግባር ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ ያለው ቢሆንም አሁንም ድረስ ዘመናዊነት የራቀውና በዘልማድ የሚካሄድ ነው። ይህም ገበያው ችግር ውስጥ እንዲወድቅ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል አንዱ መሆኑንም ይናገራሉ። የንግዱ ማህበረሰብ አሰራሩን የዘመነ እንዲያደርግ ከመንግስትና የንግዱን ማህበረሰብ ከሚመራው ምክር ቤት ብዙ እንደሚጠበቅ የገበያ ጥናት ተመራማሪው ዶክተር ጌቴ ገልፀዋል። እርሳቸው እንደሚሉት አብዛኛው የአገሪቱ ነጋዴ ማህበረሰብ የሚመራው ነገ የሚደርስበትን ዕድገት በማሰብ በእውቀት፣ ክህሎትና በገበያ ጥናት በታገዘ ስትራቴጂ አይደለም። ዘርፉ ከጊዜው ጋር ሊራመድ ከማይችል ከዚህ ተለምዷዊ አስተሳሰብ መውጣት ካልቻለ ህልውናው ዘላቂነት አይኖረውም ያሉት ተመራማሪው ይህ ደግሞ የሚጎዳው ነጋዴውን ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ ጭምር ነው ይላሉ። በመሆኑም ሁኔታውን ለመለወጥ የሚመለከተው አካል በሙሉ የበኩሉን ሚና መጫወት አለበት ብለዋል አስተያየት ሰጪዎቹ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም