የሰላም ሚኒስቴር በፅዳት ላይ ያተኮረ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ ሊያደርግ ነው

492

አዲስ አበባ ግንቦት 11/2011የሰላም ሚኒስቴር የሰላም እሴቶችን ከፅዳት ጋር በማቆራኘት የሚሰራ አዲስ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊያደርግ ነው።
የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በሁለተኛው አገር አቀፍ የፅዳት ዘመቻ ከወሎ ሰፈር አደባባይ እስከ ጎተራ ማሳለጫ መንገድ ከተቋሙ ሰራተኞችና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር አጽድተዋል።

በዚሁ መርሃ ግብር ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋማቸው የሰላም እሴቶችን ከፅዳት ጋር በማያያዝ የሚሰራ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል።

ፕሮጀክቱ በጎነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትንና ሌሎች የሰላም እሴቶችንም ጨምሮ ሊከናወንበት የሚችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በሳምንትና በወር የማከናወን አላማ ያለው መሆኑንም አስረድተዋል።

ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመተባበር እንደሚተገበር የገለጹት ሚኒስትሯ በዋነኝነት ሰላም ለሁሉም ያለውን ፋይዳ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ያከናውናል ብለዋል።

በሁለተኛው አገር አቀፍ የጽዳት መርሃ ግብር ሚኒስትሯን ጨምሮ የተቋሙ ሰራተኞች ከወሎ ሰፈር እስከ ጎተራ ማሳለጫ መንገድ ማጽዳታቸውን ሪፖርተራችን  ዘግባለች።