ለአዲስ አበባ የልማት ፕሮጀክት ሁሉም ህብረተሰብ እንዳቅሙ ሊሳተፍ ይገባል

152

ግንቦት 10/2011 የአዲስ አበባ የተፋሰስ ወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት የከተማዋን ውበት ከመጨመር ባለፈ ለነዋሪዎቿ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎችን የሚያበረክት በመሆኑ ሁሉም እንዳቅሙ ሊሳተፍ እንደሚገባ ነው  አስተያታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች የጠቀሱት፡፡

ሸገርን እናልማ ፕሮጀክት ከግንባታው ጀምሮ እስከ ሚጠናቀቅበት ድረስ ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ነው በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ክሩቤል ሀይሉ የገለጹት፡፡ 

የፕሮጀክቱ ወጭ በባለሀብት፣ በአለማቀፍ አጋሮችና በህብረተሰቡ ትብብር መሸፈኑ ሀገራዊ የልማት ተግባራት ላይ ያለውን የባለቤትነትና የተሳትፎ መንፈስ ከማሳደጉ በተጨማሪ ከመንግስት ካዝና በሚለቀቅ በጀት ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ግሽበት በማረጋጋት በኩል የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ባለሃብቶች በራሳቸው በሚያደርጉት ኢንቨስትመንት ለሀገር እድገት የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በሀገራዊ የጋራ ፕሮጀክት ላይ የሚያደርጉት ርብርብ ለሀገር እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው የገለጹት፡፡

ፕሮጀክቱ ለበርካታ አመታት ስራቸው እንደተጓተቱት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተመሳሳይ ችግር እንዳያገጥመውና ተጨማሪ ጊዜና ገንዘብ እንዳይወስድ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም ነው የጠቀሱት፡፡

ለዚህም በችኮላ ወደስራ ከመግባት ይልቅ በጥናት ላይ የተመሰረት ግልጽ እቅድ አውጥቶ መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በፕሮጀክቱ ምክንያት የሚነሱ ዜጎች ችግር ሳይገጥማቸው የተሻለ መኖሪያ አካባቢ እንዲያገኙ ማድረግ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ክሩቤል፤ ከቤት ባለቤቶቹ በተጨማሪ በርካታ ተከራይ የሚኖርባቸው  በመሆኑ እነዚሀ ዜጎች ኪራይ ቤት የሚያገኙበት ሁኔታ ሊፈጠርላቸው እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለህብረተሰቡ የሚያስገኘው ጠቀሜታ ላይ በየአካባቢው ግልጽነት የመፍጠር ስራ በመስራት ነዋሪው የበኩሉን አስተዋጽኦ በሚያደርግብት ሂደት ላይ ማተኮር ይበልጥ ውጤታማ ያደርገዋል የሚሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ ደረጄ ይርጋ ናቸው፡፡

የከተማዋን ገጽታ ጽዱ፣ ለኑሮ ሳቢ በማድረግ አረንጓዴ ቦታዎችን የመዝናኛ ቦታዎች በማድረግ ደስተኛ ትውልድ ለመፍጠር እንደሚረዳ የጠቀሱት አቶ ክሩቤል ፤ ፕሮጀክቱ የከተማዋን የቴሌ፣ የመብራትና የውሃ መሰረተ ልማቶችን በሚያዘምን መልኩ በመስራት ለሌሎች ልማቶች ምሳሌ እንዲሆን ቢደረግ መልካም ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ላቀረቡት ሀገራዊ ልማት ባለሀብቱ ያሳየው ተሳትፎ የሚያስደስት መሆኑን የገለጹት ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ መስፍን ጌታሁን፤ ሁሉም ህብረተሰብ የአቅሙን የሚያደርግበት ሆኔታ ሊመቻች እንደሚገባም ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት መዲናዋን የወንዞች ዳርቻና ተፋሰስ  ሳቢ ያልሆነ ገጽታና መጥፎ የወንዝ ሽታ ለመቀየር ትኩረት አድርጎ መነሳቱ እንዳስደሰታቸው የገለጹት  አቶ አሸናፊ ጎንፋ  በበኩላቸው፤ ለነዋሪው የቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት ላይ ግንዛቤ ማስጨበጥና ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መዲናዋ  በርካታ አህጉራዊና አለማቀፍ ተቋማት  የሚገኙባት  እንደመሆኗ ሳቢና ጽዱ አለመሆኗ የሁሉም  ጥያቄ ነው የሚሉት አቶ ተገኔ ይመር፤  በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ  መሪነት  የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር እየተደረገ ያለው  ጥረት  የወደፊት ገጽታዋን ለማየት  እንድጓጓ አድርጎኛልም ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ወንዝና ወንዝ ዳርቻዎች ልማት 29 ቢሊዮን ብር የሚፈጅ ና ከ56 ኪሎሜትር በላይ የሚሸፍን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም