በዱር እንስሳት ሀብትና መኖሪያቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ድጋፍ ያስፈልጋል

74

አዳማ ግንቦት 10 /2011ትየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዱር እንስሳት ሀብትና መኖሪያቸው ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ድጋፍ እንዲያደርጉለት የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ጠየቀ።

ባለስልጣኑ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራሮችና አባላት ጋር በአዳማ እየመከረ ነው።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በዱር እንስሳትና በመኖሪያቸው ላይ እየደረሰ ካለው ጉዳት ለመታደግ  የአባላቱ እገዛ ያስፈልገዋል።

በእንስሳቱና በፓርኮቸ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀ ነስስ የምክር ቤቱ አባላትና የቋሚ ኮሚቴ አመራሮች አሰራርና ህጎችን በማሻሻል እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

በብሄራዊ ፓርኮችና በሀብቱ ላይ እየደረሱ ካሉት ጉዳቶች መካከል ህገወጥ አደን ግጦሽና የእርሻ መሬት መስፋፋትን እንደ አብነት  አንስተዋል።

በዚህም በዱር እንስሳት መኖሪያ ፓርኮች ላይ የመመናመን አደጋ እያንዣበበ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ እንስሳትና ብርቅዬ አዕዋፍ እየተመናመኑና ወደ ጎረቤት አገሮች ጭምር እየተሰደዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዱር እንስሳት ሀብትና በፓርኮች ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር ከመሠረቱ ለማቃለል አባላቱ ግንዛቤ እንዲይዙ መደረጉ ተገቢ ነው ያሉት ደግሞ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ጫላ ለሚ ናቸው።

የፓርኮችን ወሰን ማስከበር፣ ህገወጥ ግጦሽና የእርሻ መስፋፋት ፣ ህገወጥ ሰፈራና አደን ለማስቀረት ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግም ተናግረዋል።

በበተለይም በዱርእንስሳት መኖሪያ ላይ የሚደርሰውን የሰደድ እሳት ለመከላከል ከአካባቢው ኅብረተሰብ  ጋር በደንና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ላይ በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የፓርኮቹን ጉዳትና የሀብቱን ተጋላጭነት የሚቀንስ ግብአትና ግንዛቤ ከመድረኩ እናገኛለን ያሉት አቶ ጫላ፣ ኅብረተሰቡ የጉዳዩ ባለቤት በማድረግና ችግሩን ለመፍታት እንዲረባረብ በየደረጃው ከሚገኙ ሴክተር ተቋማት ጋር መስራት ይገበል ብለዋል።

በኢትዮጵያ በሚገኙ ፓርኮችና ዱር እንስሳት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱ በተለያዩ አካላት ሲገለጽ መቆየቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም