በአዲስ አበባ ዙሪያ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተሰራ ነው ተባለ

71
አዲስ አበባ ግንቦት 29/2010 በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችን በዘላቂነት ለማቋቋምና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ። በአካባቢው በሚካሄዱ የልማት ሥራዎች ምክንያት የሚነሱ 150 አርሶ አደሮችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያቀፈና በግብርና ሥራ ላይ የሚያተኩር አክሲዮን ማህበር ተቋቁሟል። ከአንድ ዓመት በፊት "ፊንፊኔ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮችና የዳያስፖራዎች ንግድ አክሲዮን ማህበር" በሚል የተቋቋመው ማህበሩ በ180 ሚሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ካፒታል የሚንቀሳቀስ እንደሆነም ተመልክቷል። ማህበሩ የልማት ተነሺዎቹን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። የማህበሩ መስራችና የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለሚ ታዬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ የአክሲዮኑ ዋና ዓላማ አርሶ አደሮች ከይዞታቸው ሳይፈናቀሉ የአገሪቱ ህግና ደንብ በሚፈቅደው መሰረት በልማት ስራዎች ተሰማርተው እራሳቸውንና አገራቸውን እዲያግዙ  ማድረግ ነው። የአክሲዮን ማህበሩ አባላት በአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ዙሪያ በግብርና ሥራ ሲተዳደሩ የነበሩና ይዞታቸውን በቂ ባልሆነ የካሳ ክፍያ የለቀቁ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ለሚ አርሶ አደሮቹ  በሰነዶችና ማረጋገጫ ጽህፈት ቤት የማህበሩን አባልነት ካገኙ በኋላ በልማት ሥራዎች እዲሳተፉ ፍቃድ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል። የኦሮሚያ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ልጅአለም አየለ በበኩላቸው፣ አክሲዮን ማህበሩ ባቀረበው የትብብር ጥያቄ መሰረት መስሪያ ቤታቸው ግብርናን በዘመናዊ መልኩ ለመደገፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂ  ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። በውስን መሬት  ብዙ አምርቶ ሰፊውን ማህበረሰብ የመመገብ አቅም ያለው ዘመናዊ ግብርና ማስተዋወቅ ሌላኛው የማህበሩ ራዕይ እንደሆነ አቶ ለሚ ገልፀዋል። አክሲዮን ማህበሩ የአዲስ አበባን የምግብ አቅርቦት እጥረት በዘላቂነት ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ተብሏል። ከአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ይካሄዱ በነበሩ የልማት ሥራዎች በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለይዞታዎች በቂ ካሳ እንዳላገኙ በዚሁ ወቅት የተገለፀ ሲሆን አክሲዮን ማህበሩም በዋናነት የተቋቋመው በዚህ ዓይነት ችግር ውስጥ ያሉትን አርሶ አደሮች ለመደገፍ እንደሆነ ተመልክቷል። የማህበሩ መነሻ ካፒታል የተገኘው ከአክሲዮን ሽያጭና ከአባላቱ በተደረገ መዋጮ መሆኑን የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ለሚ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት አክሲዮን ማህበሩ በይዞታው የሚገኝ 40 ሄክታር የእርሻ መሬት ያለው ሲሆን በቀጣይም ማህበሩን ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል። የአክሲዮኑ አባል ለመሆን 400 ያህል የልማት ተነሺዎች ማመልከቻ ያቀረቡ መሆኑን የተናገሩት አቶ ለሚ ግለሰቦቹን አባል ማድረግ በሚቻልበት መንገድ ላይ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ከዚሁ ጎን ለጎን ማህበሩ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ በመውሰድ በከተማው ለሚኖሩ ወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያና የመዝናኛ ቦታዎችን  በአርሶ አደሮቹ ይዞታ ላይ ለመገንባት እቅድ መያዙንም ተናግረዋል። አክሲዮን ማህበሩ 150ዎቹን የልማት ተነሺ  አርሶ አደሮች ጨምሮ በጠቅላላው 178 አባላትን የያዘ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 28 የግብርና ባለሙያዎች ይገኙበታል። ከባለሙያዎቹ መካከልም ማህበሩን ለመደገፍ ፈቃደኛ የሆኑ አምስት የውጭ ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም