በክልሉ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የምሁራን ድጋፍ ያስፈልጋል ተባለ

55

በአማራ ክልል የሚታየውን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት የክለሉ ተወላጅ ልሂቃን ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተጠየቀ።

የአማራ ክልል ልሂቃን ዛሬ በአዲስ አበባ በክልላቸው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም በአገር አቀፍና በክልሉ እየተፈጠሩ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ከመልካም ዕድልነታቸው ባለፈ ፈተና እየሆኑ መምጣታቸው እየተነገረ ነው።

ግንቦት 10/2011 በዚሁ ጊዜ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮንን እንዳሉት በክልሉ እየታዩ ያሉ የልማት የመልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት ችግሮችን በትብብር ማቃለል ያስፈልጋል።

''የአማራ ክልል ህዝብ ለህግና ለእምነቱ በመገዛት የረጅም ዘመናት ታሪክ ባለቤት ነው'' ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ በቅርቡ በክልሉ እየታዩ ያሉ የሰላም እጦትና ህግን የመጣስ ዝንባሌዎች ግን ከቆየው ባህላችን ጋር የሚጣረስ በመሆኑ ማስተካከል አለብን ብለዋል።

መሰልድርጊቶች በለውጥ ሂደት የሚጠበቁ ቢሆንም ተስፋፍተው የከፋ ዋጋ እንዳያስከፍል ምሁራኑ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አንስተዋል።

የክልሉን ወጣቶች የኢኮኖሚ ማህበራዊና የፖለቲካ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም የክልሉ መንግስት ፈንድ በማፈላለግ ጭምር የተለያዩ ስራዎች ቢሰራም የሚፈለገው ውጤት ባለመምጣቱ ምሁራኑ እገዛ ማድረግ እንዳለባቸው ዶክተር አምባቸው አንስተዋል።

''በክልሉ በቅርቡ በተከሰቱ ግጭቶች ምከንያት የኮኖሚያዊ ልማት ላይ ከማተኮር ይልቅ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ቀላል የማይባል በጀት ወጥቷል'' ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ ይህን ለማካካስም ንግድና ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በአገሪቷና በክልሉ እየተፈጠሩ ያሉ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ከዕድልነታቸው ባለፈ የክልሉ ፈተና እየሆኑ መምጣታቸውንም ዶክተር አምባቸው አልሸሸጉም።

በክልሉ የሚታዩ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር፣ መቀንጨር፣ የመሰረተ ልማት አለመኖር፣ ጤናና ትምህርት እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ልሂቃኑ ያላቸውን ልምድና እውቀት በመጠቀም ችግሮቹ የሚቃለሉበትን መንገድ መጠቆም አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል ዶክተር አምባቸው።

ከአመራር ለውጥ አንዲሁም አንዳንድ አካላት በሚፈጥሩት ተጽዕኖ በክልሉ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ እጥረቶች እንደሚታዩም አንስተዋል።

ክልሉን ምቹ የመኖሪያ፣የአገልግሎትና የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግም ሁሉም የክልሉ ተወላጆች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

እንደ መንግስት መስራት የተለመደ ቢሆንም የምሁራን ተጽዕኖ የተለየ ውጤት ያመጣል ሲሉም ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የክለሉን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የድርሻቸውን ለመወጣት ፍቃደኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም