በክልሉ እየተፈጠሩ ያሉ የፖለቲካ ደርጅቶች ከዕድልነታቸው ባለፈ ስጋት እየሆኑ መጥተዋል- ዶክተር አምባቸው መኮንን

839

ግንቦት 10/2011በአገር አቀፍና በአማራ ክልል እየተፈጠሩ ያሉ የፖለቲካ ደርጅቶች ከዕድልነታቸው ባለፈ ስጋት እየሆኑ መምታቸውን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን ተናገሩ። ስጋቶችን ለመመከት የክልሉ ሊሂቃን ከክልሉ መንግስት ጎን በመቆም ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። 

በአማራ ክልል ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ የክልሉ ተወላጅ ልሂቃን  የውይይት  መድረክ አዲስ አበባ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ አየተካሄደ ነው።

ክልሉ በርካታ ቋንቋና ባህል ያላቸው ህዝቦች ተቻችለው በአብሮነት፣ በፍቅርና ወንድማማችነት ለረጅም ዘመናት የኖሩበት እንደሆነ ዶክተር አምባቸው አስታውሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአገር አቀፍና በክልሉ እየተፈጠሩ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የክልሉን ውስጣዊ አንድነትና ሰላም ለማናጋት ሲሰሩ ይስተዋላል ብለዋል።

ይህም የፖለቲካ ደርጅቶች ከዕድልነታቸው ባለፈ ስጋት እየሆኑ መምታቸውን ነው ዶክተር አምባቸው የተናገሩት።

ይህን መመከት ደግሞ የመንግሰት ብቻ ሳይሆን የክልሉ ሊሂቃን የጋራ ሃላፊነት ጭምር በመሆኑ፣ ሊሂቃን ከመንግስት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ህዝብ አንድ አይነት ስነ-ልቦና ያለው  ቢሆንም  ጥቃቅን ልዩነቶችን  በማጉላት  የሚሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዳሉ ገልጸው፤ እንዲህ አይነት ድርጊቶችን በእንጭጩ መቅጨት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የክልል መሪ ድርጅት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ክልሉን ብቻ ሳይሆን አገርን መምራት ያለበት ድርጅት መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ ግን ህዝቡ ከድርጅቱ ጋር በጋራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።