አርሶ እና አርብቶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን እንዲጠቀም ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል የመገናኛ ብዙሀን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

95

አዳማ ግንቦት 10/2011 አርሶ እና አርበቶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም ምርታማነቱን እንዲያሳድግ ግንዛቤ በማስጨበጥ በኩል የመገናኛ ብዙሀን የድርሻቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

የግብርናሚንስቴር በአዳዲስ የግብርና አሰራሮችና የልማትፓኬጅዎች ውጤታማነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ያዘጋጀው የምክክር መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።

በዚህ ወቅት የግብርና ሚንስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ እንደገለጹት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች አርሶና አርብቶ አደሩ የግብርና ልማትን ሳይንሳዊ በሆኑ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች እንዲመራ በሙያቸው  ማገዝ አለባቸው።

የዘርፍን ልማት ለማፋጠን የሚያግዙ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችና አሰራሮች ዙሪያ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም  የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የግብርና ልማትና እድገት ግቡን እንዲመታ የሰው ኃይል የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም በግንዛቤና ክህሎት ማገዝና ውጤታማ ለማድረግ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ከዘርፉ ተቋማት ጋር በትብብር የሚተጋገዙበት አሰራር እየተዘረጋ ነው።

“የመሬትአጠቃቀም በአርሶ አደሩ ዘንድ እንዲሻሻልና  ምርታማነት እንዲያድግ  በሚቻልበት ሂደት ላይ  ግንዛቤ በማስጨበጥ ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።

በሚኒስቴሩ የወተት ልማት ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ተካ በበኩላቸው ባለፉት አስር ዓመታት በኤክስቴሽን አገልግሎት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂና አሰራሮችን በማመንጨት በእንስሳትና ሰብል ልማት ዘርፍ  የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

በእንስሳት ልማት ዙሪያ በምርምር ማዕከላት የወጡ አዳዲስ ግኝቶች  አርሶ አደሩ ዘንድ እንዲደርሱ በማድረግ በኩል የተሻለ አፈፃፀም መኖሩን ተናግረዋል።

በሰብል ልማት በተለይም የስንዴ፣ገብስ፣ ሽንብራ፣በቆሎና ማሽላ ምርታማነት በአማካይ በሄክታር ከ29 እስከ 39 ኩንታል መድረሱን ጠቅሰውይህንን ይበልጥ  አጠናክሮለማስቀጠል የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የአርሶአደሩን ግንዛቤ የማሳደግ  ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል።

በውጭ ምንዛሪ የሚገባውን የእህል ግዥ በሀገር ውስጥ ለመተካት ቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራሮችን በተገቢውን መንገድ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆኑም እንዲሁ።

ሳይንሳዊ አሰራር የተከተለ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ለማከናወን፣የምርምር ውጤቶች ከአካባቢው የአየር ፀባይ ጋር ተስማሚ መሆናቸውን የመፈተሽ ብሎም አርሶና አርብቶ አደር የሚፈለገውን ውጤት ማምጣታቸውን ጭምር የድርሻቸውን እንዲወጡ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረኩ ከፌዴራልና ከክልል መገናኛ ብዙሃን  ተቋማት የተወጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም