አንድ ቀን ለቀረው የ’ሸገር ገበታ’ ማዕድ ለመቋደስ ክፍያ የሚፈጽሙ ድርጅቶች ተሳትፎ ቀጥሏል

457

ግንቦት 10/2011 ለሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት ገቢ ማሰባሰቢያ ለተዘጋጀው የ’ሸገር ገበታ’ ማዕድ ለመቋደስ ክፍያ የሚፈጽሙ ድርጅቶች ተሳትፎ ቀጥሏል፤ አስካሁንም 1 ነጥብ 275 ቢሊዮን ብር ገቢ ተደርጓል። 

ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት ለመጠናቀቅ አንድ ቀን በቀረው የ’ሸገር ገበታ’ ማዕድ ተሳታፊዎች ክፍያ የሚከፍሉበት ሂደት 6ኛ ዙር ደርሷል።

በስድስተኛው ዙርም ከ18 ያላነሱ የተለያዩ ኩባንያዎች ለ’ሸገር ገበታ’ ራት ክፈያ የፈጸሙ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት የመኖሪያ ጉዳይ ድርጅት 3 ሚሊየን ዶላር፣ የመንግስትቱ የእርሻና ምግብ ድርጅት ደግሞ 400 ሺህ ዶላር ድጋፍ ማድረጋቸው ተመልክቷል።

ቀደም ሲል በነበሩ አምስት ዙሮች በመጀመሪያው ከ34፣ በ2ኛው ከ20፣ በ3ኛው ከ38፣ በ4ኛው ከ12፣ በ5ኛው ከ20 በላይ ተቋማትና ግለሰቦች የተሳትፎ ድጋፍ ማድረጋቸውን የጽህፈት ቤቱ ቲዊተር ገጽ ያሳያል።

የሸገር የወንዝ ዳር ፕሮጀከት 56 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን 29 ቢሊየን ብር ወጭ ይደረግበታል።

እስካሁን ባለው መረጃ መሰረትም ከ255 ተቋማትና ግለሰቦች በእራት ግብዣው ለመሳተፍ የተመዘገቡ ሲሆን 1 ነጥብ 275 ቢሊዮን ብር ገቢ መደረጉ ታውቋል።

በእለቱ መርሃ ግብሩ ላይ ለመካፈል መቀመጫ የገዙ አካላት ቤተ መንግስትን የሚጎበኙ ሲሆን ምሽት ላይም በሚዘጋጀው የእራት ስነስርዓት ለመካፈል እስካሁን ባለው መረጃ ከ255 በላይ ተቋማትና  ግለሰቦች በገንዘብና በተለያየ ደረጃ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

የእራት ድግሱ የሚካሄደው በ132 እድሜ ባስቆጠረው የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ቤተ-መንግስት አዳራሽ ነው።