በመጪው ክረምት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቋመ

70

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2011 በኢትዮጵያ በመጪዎቹ የክረምት ወራት የሚፈጥርን የእርጥበት መጨመር ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ አስቀድሞ  ለመከላከል ግብረ ኃይል መቋቋሙን የብሄራዊ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ዋና ዋና የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች በጥናት መለየታቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል።  

በኢትዮጵያ ከአየር ለውጥ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ በሚከሰት ቅጽበታዊ ጎርፍና ተያያዥ አደጋዎች ሳቢያ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት ይደርሳል።

በዘንድሮ በልግ ወቅት  በኦሮምያ፣ ደቡብ፣ አፋርና ጋምቤላ አንዳንድ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ  መድረሱ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው።

በተለይ ሰሞኑን በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን የደረሰው አደጋ 5 ሺህ 630 ሰዎችን ለጉዳት የዳረገ ሲሆን  700 ቤቶች ፈርሰዋል፤ ከቤቶቹ መካከልም 60 የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመለክታል። 

በኮሚሽኑ የቅድመ ማስጠንቀቂያና አስቸኳይ ግዜ ምላሽ ዳይሬክተር ወይዘሮ አልማዝ ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤በበልጉ ባለፉት ወራት የደረሰው የጎርፍ አደጋ ከክልሎቹ አቅም በላይ ሆነው ባለመገኘታቸው ያለፌደራል ድጋፍ በእራሳቸው አቅም ችግሩን መከላከልና ሰለባዎቹንም መታደግ ችለዋል።    

"በስልጤ ዞን ላይ የደረሰው ችግር ግን የኛን እርዳታ የጠየቀ ነበር፤ እናም አስፈላጊውን የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፍ ተደርጓል" ብለዋል። 

እንደ ወይዘሮ አልማዝ ገለጻ በቀጣዩ የክረምት ወቅት እርጥበትና የዝናብ መጠን የሚጨምር በመሆኑ ቅጽበታዊ ጎርፍ አደጋን አስቀድሞ ለመከላል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው። 

በአሁኑ ወቅት አዋሽ ተፋሰስ፣ ድሬዳዋ፣ መካከለኛውና ደቡብ ምስራቅ ትግራይ፣ በአማራ ደቡብና ሰሜን ወሎ እንዲሁም ኦሮሚያ ልዩ ዞን ቅጽበታዊ የጎርፍ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችል በጥናት መለየቱን አስታውቀዋል። 

በተመሳሳይም በአፋር ዞን 1፣ 2፣ 4፣ በኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ አካባቢ በደቡብ ክልል ሀድያ፣ ስልጤና ጉራጌ እንዲሁም ሲዳማ የጎርፍ አደጋው ተጋላጭ መሆናቸውን  ዳይሬክተሯ ወይዘሮ አልማዝ አክለዋል።

በሱማሌ ክልል ጅግጅጋም ተመሳሳይ ቅጽበታዊ ጎርፍ ይደርስባቸዋል ተብሎ ከተለዩ ቦታዎች መካከል እንደሆነ አመልክተዋል።

ችግሩን በተደራጀ መንገድ ለመከላከል ይቻል ዘንድም ከውኃ፣ ግብርና፣ ትምህርትና ጤና ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጣ ግብረ ኃይል የተቋቋመ ሲሆን መንግታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም የግብረ ኃይሉ አባል መሆናቸውን ያብራራሉ።   

ወይዘሮ አልማዝ እንደሚሉት ግብረ ኃይሉ የብሄራዊ ሚትዮሮሎጂ የሚሰጠውን ትንበያ መሰረት በማድረግ የትኞቹ አካባቢዎች ሊጠቁ ይችላሉ፣ የት አካባቢ የትኛው ሴክቴር መስሪያ ቤት ጣልቃ በመግባት ድጋፍ ማድረግ አለበት፣ ምን አይነት የመፍትሄ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው የሚለውን የመጠባበቂያ እቅድ ያዘጋጃል። 

ክልሎችም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚዘጋጀውን የመጠባበቂያ እቅድ ወስደው ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥመው እንዲጠቀሙበት ይደራጋል የሚሉት ወይዘሮ አልማዝ የክልሎች ግብረ ኃይልም ይቋቋማል ብለዋል።  

የፍሳሽ ቦዮችን በቆሻሻና ባዕድ ነገሮች መሙላት የጎርፍር አደጋውን ከሚያባብሱት ምክንያቶች መካከል በመሆኑ  ኀብረተሰቡ መሰል ድርጊቶችን ከማድረግ መቆጠብ እንደሚገባው አሳስበዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም