በወልድያ በ18 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የማርና ማር ውጤቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ

230

ወልድያ ግንቦት  10 /2011ወልድያ ከተማ በ18 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የማርና ማር ውጤቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ።

”የጁ” ተብሎ የተሰየመው ፋብሪ በቀን 32 ኩንታል ማር የማቀነባበር አቅም እንዳለው የፋብሪካው የፕሮጀክት ኤክስቴንሽንና የግብአት ቁጥጥር ባለሙያ አቶ አርአያ ገላው ለኢዜአ አስታውቀዋል።

የጥረት ኮርፖሬት ንብረት የሆነው ፋብሪካ ለጊዜው በአንድ ፈረቃ ብቻ 16 ኩንታል ማር ማቀነባበር መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በቅርቡም በሁለት ፈረቃዎች በማሰራት ሙሉ አቅሙን ለመጠቀም ጥረት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በወልድያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ወስጥ የተቋቋመው ፋብሪካ በአሁኑ ወቅት ለ32 የወጣቶች ሥራ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

ምርቱን በግማሽ፣ በአንድ ኪሎ ግራምና በአንድ ኪሎ ግራም ተኩል መጠን በማዘጋጀት ለባህር ዳርና ለአዲስ አበባ ከተሞች እንደሚያቀርብ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም ከምርቱ ገሚሱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱን አቶ አርአያ ገልጸዋል፡፡

በፋብሪካው ሥራ ከተቀጠሩት መካከል ወጣት ኤፍሬም ዓለሙ በበኩሉ በማሽን ኦፕሬተርነት ተቀጥሮ በወር 2ሺ ብር እየተከፈለው ሶስት ቤተሰቡን እያስተዳደረ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በላስታ ወረዳ የቀበሌ 23 ነዋሪና ማር አምራች የሆኑት አርሶ አደር እንዳየነው ወርቀልዑል በበኩላቸው  ምርታቸውን በብዛትም በጥራትም በማምረት ለፋብሪካው በማውቅረብ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡

በጉባላፍቶ ወረዳ የቀበሌ 15 ነዋሪ አርሶ አደር ሰሜ ምላሹ በበኩላቸው ፋብሪካው ሥራ በመጀመሩ ምርታቸውን በተሻለ ዋጋ በመሸጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡