የሱዳን የፖለቲካ ሽግግር ስኬታማ እንዲሆን ድጋፌን እቀጥላለሁ – ኢጋድ

241

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2011 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ)  የሱዳን የፖለቲካ ሽግግር በስኬት እንዲጠናቀቅ የጀመረውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገለፀ። 

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልኩት ነው ብሏል።

ኢጋድ ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፤ በሱዳን የፖለቲካ ኃይሎች የፖለቲካ ሽግግር ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑን ገልጿል።

ከዚህ በኋላም የሱዳን ሕዝብ ፍላጎትን ለማሟላት ፖለቲከኞቹ የጀመሩትን ምክክር በስኬት ያጠናቅቃሉ የሚል ተስፋ አንዳለው ኢጋድ አስታውቋል።

ምክክሩም በትብበር መንፈስ ተቃኝቶ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኩራል ተብሎ ይጠበቃል።

በቅርቡ በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ኢጋድ ባካሄደው 67ኛ ልዩ ስብሰባው የኢጋድ አባል አገራት በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ሥር በመሆን በሱዳን ጉዳይ ላይ በጣምራ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ኢጋድ ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በጋራ በመቆም የሱዳን የፖለቲካ ሽግግር ስኬታማ አንዲሆን እሰራለሁ በሏል በመግለጫው። 

በሱዳን የተካሄደውን ወራትን የወሰደ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል በመወሰው እርምጃ አገሪቱን ላለፉት 30 ዓመታት የመሩትን ኡመር አልበሽር ከስልጣን አውርዷል።

በአሁኑ ወቅትም አገሪቱን የሚመራው በጦሩ የተሰየመው ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ነው።