የጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎች ከሙያ ተቆርቋሪነት የመነጩ ናቸው…ዶክተር አሚር አማን

86

ግንቦት /2011 በጤና ባለሙያዎች እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች የጤና ዘርፉን የአገልግሎት አሰጣጥ በፍጥነት ለማሻሻል ከሙያ ተቆርቋሪነት የመነጩ ምክንያቶች ናቸው ሲሉ የጤና ሚኒስትሩ ተናገሩ።

የጤና ባለሙያዎቹ ጥቅማጥቅም ይከበር በሚልና በጤና ተቋማት የሚስተዋል የግብዓት ችግር ይፈታ ሲሉ ጠይቀዋል።

የጤና ባለሙያዎች በሚያነሱቸው ጥያቄዎች ዙሪያ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በባህርዳር ከተማ ዛሬ ተወያይተዋል።

ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በውይይቱ ላይ እንደገለፁት በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ቅንነት የተሞላባቸው ናቸው።

ባለሙያዎቹ በጤና ተቋማት መድሃኒት የለም፣ ህሙማን ወለል ላይ መተኛት የለባቸውም፣ የህክምና መሳሪያ ይሟላ፣ ተገቢው ባለሙያ ይመደብ የሚሉትና መሰል ጥያቄዎች የታካሚዎች ችግር እንዲፈታ ከሙያ ተቆርቋሪነት የመነጨ እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለሙያዎቹ ጥቅማ ጥቅማችን ይከበር ማለታቸውም ቢሆን ሙያዊ ፍቅራቸውን ሳይሰስቱ እንዲሰጡና የተነሳሽነት ችግሮች እንዲፈቱ ከማሰብ እንደሆነም አብራርተዋል።

“እነዚህን ጥያቄች መንግስት በፍጥነት በመመለስም በጤናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች እንዲፈቱ ገፊ ምክንያቶችና ጤነኛ ጥያቄዎች ናቸው” ብለዋል።

በመሆኑም ጥያቄዎች በመመሪያና በፖሊሲ፣ በአሰራርና በጥቅማጥቅም የተጠቃለሉ መሆናቸውን ጠቅሰው አላሰራ ያሉ መመሪያዎችና ደንቦች በጥናት ተለይተው እንዲሻሻሉ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በላቦራቶሪ እቃዎች፣ በመድሃኒትና በሌሎች የህክምና መሳሪያዎች ይስተዋል የነበረውን የግዥ ስርዓት በመቀየርም ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ከካምፓኒዎች ጋር ውል በመፈፀም ቀልጣፋ አሰራር መዘርጋቱን ጠቅሰዋል፡፡

የባለሙያዎቹ ጥቅማ ጥቅሞችም ከዚህ ወር ጀምሮ ለተመሳሳይ ሙያ ተመሳሳይ ክፍያ መፈቀዱን ጠቅሰው “ህብረተሰቡን የሚያረካ የጤና አገልግሎት ለመስጠትም አላሰራ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ቀጣይ ስራዎች ይሰራሉ” ሲሉ ዶክተር አሚር አስታውቀዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አበባው ገበየሁ በበኩላቸው እንደገለጹት የጤና ባለሙያዎች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ጥረት ይደረጋል፡፡

እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎችንም በስራ ላይ እንቅፋት እንዳይፈጥር በቀጣይ በየደረጃው ከሚገኙ ባለሙያዎች ጋር ለማወያየት ጥረት ይደረጋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር ዶክተር አምባቸው መኮነን በበኩላቸው “የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ ለመፍታት ክልሉ አቅም በመፈቀደ መጠን ጥረት ያደርጋል”ብለዋል።

“አሁን ላይ የጤና ባለሙያዎች እየተከፈላቸው ያለው ባገለገሉትና በሚከፍሉት መስዋትነት ልክ ሳይሆን በመክፈል አቅም ልክ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል።

የገንዘብ ጥያቄ እንዳለ ሆኖ የጤና ባለሙያዎች እርካታ የሚመጣው አክመው በሚያድኑት የሰው ህይወት እንጂ በሚከፈላቸው ገንዘብ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

“አሁን ያለንበት ወቅት ፈታኝ ነው” ያሉት ዶክተር አምባቸው የባለሙያዎቹ ጥያቄዎች ከገንዘብ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው የመክፈል አቅምን ባገናዘበ መንገድ መንግስት ለማሟላት ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

በውይይቱ የተገኙት ሲስተር ፍሬህይወት ቀናው በበኩላቸው ውይይቱ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎች በዘላቂነት ይፈታሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

“በመተማ ሆስፒታል የግላብና ሌሎች የህክምና መሳሪያዎች ጉድለት በመኖሩ ተቸግረናል” ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ አንዳርጋቸው ክንዱ ናቸው፡፡

በውይይቱ የችግሩን ስፋት በመረዳት መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ይፈታዋል የሚል እምነት እንዳላቸውና መግባባት እንደተደረሰም ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ጤና ባለሙያዎች ፕሬዝዳንት ሻለቃ ፈንታየ አወቀ በበኩላቸው “ውይይቱ የባለሙያዎችን ጥያቄ በተደራጀ አግባብ ለመፍታት ያስችላል” ብለዋል፡፡

በውይይቱ ከተለያዩ የህክምና ተቋማት የመጡ ባለሙያዎችና አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም