የምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላደረሰብን በደል መፍትሔ ይሰጠን---የፍርድ ቤቱ የአስተዳደር ሰራተኞች

77

ግንቦት 9/2011 በምስራቅ ጎጃም ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአስተዳደር ሰራተኞች ፍርድ ቤቱ የመልካም አስተዳደር በደል አድርሶብናል ሲሉ ተቃውሟቸውን ገለጹ።

ሰራተኞቹ ደርሶብናል ያሉት በደል የፍርድ ቤቱ ዳኛ ላስተላለፉት የክፍያ ትዕዛዝ ህጋዊ አሰራርን እንዲከተል በጠየቀች የስራ ባልደረባቸው ላይ የእስር ቅጣት መወሰናቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ስራ በማቆም ተቃውሟቸውን የገለጹት ሰራተኞቹ አንድ የፍርድ ቤቱ ዳኛ በተቋሙ የሒሳብ ሰራተኛ ላይ ያለአግባብ የ10 ቀን እስራት ወስነዋል በሚል ነው።

ከሰራተኞቹ መካከል ወይዘሮ ማናየሽ የሻነህ ለኢዜአ እንደገለፁት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ለጨረታ አጫራቾች የውሎ አበል እንዲከፈል የሰጡትን ትዕዛዝ ለመፈጸም ህጉን ተከትሎ የመገጣጠሚያ ደብዳቤ እንዲጻፍ በመጠየቋ ብቻ ባልደረባቸው ለእስር ተዳርጋለች።

በዚህም ምክንያት አሰራርን መሰረት ባለደረገ አግባብ በጫና እንድትፈፅም ዳኛው ማስገደዳቸው አግባብ ባለመሆኑ መብታቸውን ለማስከበር ተቃውሟቸውን መግለጻቸውን ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ባንቻየሁ ለገሰ የተባሉ ሌላዋ ሰራተኛ በበኩላቸው የአሰራር ክፍተት ሳይኖር የእስር ትዕዛዝ መሰጠቱ አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ስህተት ቢኖር እንኳ በሰራተኛ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት መቅጣት ሲገባ ስልጣንን መከታ በማድረግ በእስር መቅጣት አግባብ ባለመሆኑ ተቃውሟቸውን በአድማ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ ብርሃኑ አንድ ዳኛ ጥፋተኛ ነው በማለት የሰጠውን ውሳኔ መሻር እንደማይችሉ ገልጸው የዚህ አይነት ጉዳይ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚታይና ይግባኝ የሚባልበት በመሆኑ እልባት እንዲያገኝ እንደሚደረግ አስረድተዋል።

ሰራተኞቹ ተቃውሟቸውን አቁመው ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲገቡ ውይይት እየተካሄደ ቢሆንም ለጥያቄያችን ተገቢውን ምላሽ ካላገኘን አንቀበልም ማለታቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም