ፓርኩ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘትና ሥራ በመፍጠር አስተዋፆው እንዲጎለብት ድጋፍ ይደረግለታል

291

ሐዋሳ ግንቦት /2011 የሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና ለአካባቢው ማህበረሰብ ሥራ በመፍጠር እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ እንዲጠናከር ድጋፍ እንደሚያደርግለት የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ 

የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔና አመራሮች ከፓርኩ  ኃላፊዎች ጋር ትናንት ተወያይተዋል ።

የከተማው ምክትል ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሹዳ በወቅቱ እንደገለጹት ፓርኩ በሚያመርታቸው የውጭ ንግድ ምርቶች የአገሪቱ ውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲያድግ አስተዋፆ እያበረከተ ነው ።

ለአካባቢው ማህበረሰብ ሥራ ከመፍጠር ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እያበረከተ መሆኑንም ተናግረዋል ።

“ይሁን እንጂ የአካባበቢው ማህበረሰብ ስለ ፓርኩ በቂ ግንዛቤ ባለመያዙ የልማቱ አጋዥ መሆኑን በወል አልተረዳም” ያሉት አቶ ስኳሬ፣ በግንዛቤ እጥረት እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።

ሰራተኞች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ተከትሎ በአንዳንድ አካላት አካባቢው ሰላም የሌለው ለማስመሰል እየተደረጉ ባሉ እንቅሰቃሴዎች በፓርኩ የተሰማሩ ባለሀብቶች ስጋት እንዳይገባቸው ማድረግ የውይይቱ ዓላማ መሆኑን ተናግረዋል ።

“በፓርኩ በሰራተኞች የሚነሱ የደሞዝ ክፍያ ቅሬታ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ አማካኝነት በጥናት የሚመለስ ነው” ያሉት ምከትል ከንቲባው፣ ፓርኩ ሰላማዊ የኢንዱስትሪ መንደርነቱን  እንዲያጠናክር አስተዳደሩ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍጹም ከተማ በበኩላቸው ለፓርኩ ልማት ውጤታማነት የአካባቢውን ህብረተሰብ ከሚመራ የመንግስት አካል ጋር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ።

“ፓርኩ ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ስራ እድል ፈጥሯል”ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የሰው ኃይሉን ታሳቢ ያደረገ የጤና አገልግሎት የሚሰጥ ጤና ተቋም በከተማው አስተዳደር አማካኝነት ለማቋቋም ከስምምነት መደረሱን አመልክተዋል ።

“ፓርኩ ከባለሃብቱ፣ ከከተማው አስተዳደርና በስሩ ከሚገኙ ተቋማት ጋር በመገኛኘት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ይሰራል” ብለዋል ።

 ዶክተር ቲሮ ታደለ የተባሉ የመድረኩ ተሳታፊ በፓርኩ በተመለከተው የሶስት ኩባንያዎች የስራ እንቅስቃሴ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

“ፓርኩ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሬ ገቢ በማሳደግና ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሥራ እድል በመፍጠር እያበረከተ ያለውን አስተዋፆ  ለማጠናከር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባዋል”ሲሉ ተናግረዋል።

አቶ ደስታ ዳንቻ የተባሉ የአስተዳደሩ አመራር በበኩላቸው መንግስት ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት የፓርኩ ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

“የሐዋሳ ኢንዱትሪ ፓርክ ከፈጠረው የስራ እድል በተጨማሪ በዘርፉ የሚደረገውን የቴክኖሎጂ ሽግግርን መረዳትና እንደ አመራር ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ “

ፓርኩን በተመለከተ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ አመራሩ ሚናውን ይወጣል ብለዋል ።

ፓርኩ ለ25 ሺህ ዜጎች ሥራ የፈጠረ ሲሆን፣ 21 ኩባንያዎች በማምረት ላይ መሆናቸው ታውቋል ።