የሚዲያ አካላት በአዕምሮ ህመም ላይ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ እንዲያሳድጉ ተጠየቀ

50

አዳማግንቦት 9/ 2011 የሚዲያ አካላት በአዕምሮ ህመም ላይ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በሚያሳድጉ ተግባራት ተሳትፏአቸውን እንዲያሳድጉ የአማኑኤል አእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አሳሰበ።

በሆስፒታሉ አዘጋጅነት የሚዲያና የጥናታዊ ጽሁፍ ፎረም የድርጊት መርሃ ግብር ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢዳኦ ፈጆ የሚዲያአካላቱ ከሕመሙ የተነሳ የሚመጣ ጉዳትና ሞትን ለመቀነስ ሚናቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ በአዕምሮ ጤና ችግር እየተስፋፋ የመጣውን ሕመም በመከላከል ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ከአገሪቱ ሕዝብ እስከ 17 በመቶ የሚሆነው ችግሩ  እንደሚታይበት  በጥናት መረጋገጡንም አመልክተዋል።

ኅብረተሰቡ ታማሚዎቹን በጊዜ ወደ ጤና ተቋም በመውሰድ በቀላሉ እንዲፈወሱ ከማድረግ ይልቅ ሸሽጎ በቤት ውስጥ በማዋል ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየተዳረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ስፔሻሊስት ዶክተር ዮናስ ላቀውበበኩላቸው በአገሪቱ ከሚገኙ የአእምሮ ታማሚዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ወደ ጤና ተቋም ሄደው አይታከሙም ይላሉ።

በዚህ ምክንያት በየዓመቱ ከ7 ሺህ 700 የሚበልጡ የአእምሮ ህሙማን የራሳቸውን ሕይወት እንደሚያጠፉ በጥናትመረጋገጡን ገልጸዋል።

ጉዳቱ ለመከላከል በተቀናጀ መልኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል ያሉት ዶክተር ዮናስ፣ በተለይ መንግሥት  ልዩ ትኩረት በመስጠትና በቂ በጀት መመደብ ይገባዋል ብለዋል።

በተለይ ሚዲያው በማኅበረሰቡ ዘንድ በበሽታው ያለውን የተዛባ ግንዛቤ ለመቀየር  ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በሆስፒታሉ ከፍተኛ የሥነ አእምሮ ህክምና ባለሙያ አቶ አስራት ጫካ ሆስፒታሉ በምስራቅ አፍሪካ ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት የሚሰጥ፣በእዕምሮ ጤና ህክምና እንዲሁም በአእምሮ ጤና ምርምርና ስልጠና የልህቀት ማእከል ተቋም  ለመሆን ራዕይ ሰንቆ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓመት እስከ 150 ሺህ ተመላላሽና ለ2 ሺህ 800 የአእምሮ ጤና ታማሚዎችን በማስተኛት የህክምናና የተሀድሶ ጤና አገልግሎትን በመስጠት ከህመሙ የተነሳ የሚመጣ ጉዳትና ሞትን ለመቀነስ ጥረት እያደረገ መሆኑንም  አብራርተዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የአዕምሮ ጤና ምንነት፤ በአዕምሮ ጤና ላይ የማኅበረሰቡ የግንዛቤ ደረጃ፤ በአገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የስርጭት የሚመለከት ገለፃ ተደርጓል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው በዚሁ መድረክ ላይ የህትመትና የብሮድካስት ሚዲያ አካላትና የጤና ዘርፍ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በመሳተፍ ፎረሙን በአዲስ መልክ አዋቅረዋል።

ጤና ሚኒስቴር የሚተዳደረው የአማኑኤል አዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኢትዮጵያ ውስጥ የአዕምሮ ህክምና የሚሰጥ ሲሆን፥የተቋቋመውም በጣልያኖች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1937 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም