በመሎ ኮዛ ወረዳ በተከሰተ የተቅማጥ በሽታ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ

242

አርባምንጭ ግንቦት 9/ 2011 በጎፋ ዞን በመሎ ኮዛ ወረዳ በተከሰተ የተቅማጥ በሽታ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ገብረ ለኢዜአ እንዳስታወቁት  ባለፉት አራት  ቀናት በወረዳው ጋይና በሚባል ቀበሌ ውስጥ  ከውሃ ብክለት ጋር በተያያዘ በተከሰተው በሽታ ህይወት ቀጥፏል።

በበሽታው የተያዙ ሌሎች 34 ሰዎች በጤና ባለሙያዎች አስቸኳይ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በሽታው የተከሰተው በአከባቢው የጣለው ከፍትኛ ዝናብ ኅብረተሰቡ ለመጠጥ የሚጠቀምባቸውን ምንጮች በመበከሉ  ነው። በአከባቢው የአደጋ ጊዜ ጤና ቡድን መሰማራቱን ጨምረው ኃላፊው  አስረድተዋል።

ችግሩን ለመቅረፍም ከወረዳው ውሃና ማዕድን ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር የመጠጥ ውሃ ምንጮችን በክሎሪን መታከማቸውንም አመልክተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃውን አፍልቶ እንዲጠቀም በመደረግ ላይ  መሆኑንም አቶ ጥላሁን ተናግረዋል።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉነህ አውሳቶ በበኩላቸው ለችግሩ ምላሽ በመስጠቱ በበሽታው የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ገልጸዋል።

በአካባቢው በተሰማራው ቡድን በሽታው በአስተማማኝ ሁኔታ ቁጥጥር እስኪውል ድረስ እንደሚቆዩ አስታውቀዋል ፡፡

የነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ በዘላቂነት ለመፍታት በ2012 የበጀት ዓመት የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ለማከናወን መታሰቡንም አመልክተዋል።