በሀገሪቱ የስፖርት ሳይንስ በመጠቀም ዘርፉን ለማሳደግ ዩኒቨርስቲዎች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው—የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን

317

ግንቦት  9/2011 በሀገሪቱ የስፖርት ሳይንስ በመጠቀም ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በተጣጣመ መልኩ ዘርፉን ለማሳደግ ዩኒቨርስቲዎች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ገለጸ።

ስፖርቱን  ህዝባዊ መሰረት ለማሲያዝ የሚቻልበት ላይ የሚመክር ሀገር አቀፍ የስፖርት አውደ ጥናት ዛሬ በወለጋ ዩኒቨርስቲ ተጀምሯል።

የፌዴራል ስፖርት ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው ባልቻ በዚህ ወቅት እንዳሉት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ሳይንስ ትምህርት በጥናትና ምርምር ስራዎች መደገፍ አለባቸው።

ዘርፉ ሌሎች የትምህርት መስኮች የደረሰቡትን የእድገት ደረጃ  ከማብቃት  አኳያ ከተቋማቱ  ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በተለይም የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ባለሙያዎችን በጥራትና በብዛት በማፍራት ድርሻቸው ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ የዘርፉን ሳይንስ ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በተጣጣመ መልኩ ለማሳደግ ሚናቸው ከፍተኛ ነው።

በዩኒቨርስቲዎች የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች የወቅቱን የሀገሪቱን የስፖርት ልማት ግቦችን የሚፈታተኑ ችግሮችን የሚፈቱ እንዲሆኑ የሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ከአውደ ጥናቱ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

የወለጋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ዶክተር ሀሰን ዩሱፍ  በበኩላቸው  ከህብረተሰቡ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ትስስር በመፍጠር የስፖርቱን ዘርፍ ልማት ለማጠናከር  እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው አውደ ጥናቱ በዘርፉ ዙሪያ በሚቀርቡ ጥናቶች ላይ በመወያየት ለችግሮቹ የመፍትሄ ሀሳቦች ይጠበቃል።

ከፌዴራል እና ኦሮሚያ ክልል ስፖርት ኮሚሽኖች፣ ከሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በአውደ ጥናቱ እየተሳተፉ ነው።