በኤሌትሪክ ሃይል እጥረት ምከንያት የፈረቃ አገልግሎት ተጀመረ

104

አዲስ አበባ ግንቦት 9/2011 በደቡብና በምስራቅ የአገሪቷ ክፍል በሚገኙ ግድቦች ላይ የውኃ መጠን መቀነስን ተከትሎ ያጋጠመውን የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ለማቃለል የፈረቃ አገልገሎት መጀመሩን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ሰሞኑን በአገር ደረጃ የነበረውን የኤሌትሪክ ሃይል መቆራረጥ አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የውሃ መስኖና ኢኒርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በሰጡት ማብራሪያ በአገር  አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኃይል መቆራረጥ ለማቃለል የፈረቃ አገልግሎቱ ተጀምሯል።

የፈረቃ አገልግሎቱ የተጀመረው ከግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እንደሆነና እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም እንደሚቆይ ተገልጿል።

ሰሞኑን የኤሌትሪክ ሃይል መቆራረጥ የተከሰተው በመልካ ዋከና፣ በጊቤ ሶስትና በቆቃ ግድቦች ያለው የውሃ መጠን በመቀነሱ ምክንያት እንደሆነ አስታውቀዋል።

በተለይም የጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ አቅም 5 ሺህ 940 ጊጋ ዋት  ይሆናል ተብሎ ባጋጣመው የውኃ መጠን መቀነስ አሁን ላይ 4 ሺህ 916 ጊጋ ዋት ላይ መድረሱ ተጠቅሷል።

በግድቦቹ የውሃ መጠን መቀነስ በማጋጠሙ ምክንያት የ426 ሜጋ ዋት የሃይል እጥረት በማስከተሉ ምክንያት የፈረቃ አገልግሎቱ መጀመሩም ተመልክቷል።

የፈረቃ አገልግሎቱ በቀን ለሶስት ጊዜ ከጠዋቱ አንድ ሰአት እስከ አምስት ሰአት፣ ከአምስት ሰአት እስከ 10 ሰአት፣ ከቀኑ አስር ሰአት እስከ ምሽቱ አራት ሰአት ተግባራዊ የሚሆን ነው።

ሚኒስቴሩን ጨምሮ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ያቀፈ የፈረቃ አገልግሎቱን የሚያስፈጽም ብሔራዊ ግብረ ሃይል መቋቋሙም ተጠቅሷል።

የፈረቃ አገልግሎቱ በዩንቨርስቲዎች፣ በማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የመድሐኒት ፋብሪካዎች፣ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችና በኤክስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት ላይ ተግባራዊ እንደማይሆንም ሚኒስትሩ አመልክቷል።

የበልግ  የዝናብ መጠን በመቀነሱ  የተጀመረው የፈረቃ ሥርዓት የሚቆየው በክርምት  ወር የሚጠበቀው የውኃ አቅርቦት እስኪሟላ ድረስ መሆኑም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም