ምክር ቤቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ በሚደረገው ሂደት ክትትሉን ያጠናክራል ተባለ

58

ግንቦት 9/2011  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው ለመመለስ በሚደረገው ሂደት ክትትሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

ምክር ቤቱ የሚያዚያ ወር የስራ እንቅስቃሴውን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ምስራቅ መኮንን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት ምክንያት በርካታ ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።

ምክር ቤቱ ከአስፈጻሚ አካላትና ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በመሆን ተፈናቃይ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በዚህም በየአካባቢው ተጠልለው ለሚገኙና እርዳታ ለሚሹ ተፈናቃይ ዜጎች በቅርበት ክትትል የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።

ዜጎችን ወደ ቀያአቸው እንዲመለሱ ለማድረግና ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸው በሚደረገው እንቅስቃሴ ምክር ቤቱ ክትትል ያደርጋል ተብሏል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ስራዎችንም የማጠናከር ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከእንግሊዝ፣ ከሰርቢያ፣ ኒውዝላንድ፣ ከሳውዲ አረቢያና ሌሎችም አገራት ጋር የፓርላማ ግንኙነትን የማጠናከር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ምክር ቤቱ በሚያዚያ ወር ከቀረቡ 12 ረቂቅ አዋጆች ውስጥ 5ቱ ጸድቀው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታውቋል።

ሰባት የሚሆኑትን ደግሞ ለቋሚ ኮሚቴዎች ለዝርዝር እይታ ተልከዋል ተብሏል።

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማቋቋሚያ አዋጅ፣ ከስዊዝ መንግስት ጋር የተፈረመው የአየር አገልግሎት ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅና ለምስራቅ አፍሪካ የክህሎት ሽግግርና ክልላዊ ትስስር ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ከአለም አቀፍ የልማት ማህበር ጋር የተፈረመው የብድር ስምምነት ማጽደቂያ አዋጅ የጸደቁ አዋጆች ናቸው።

ከጅቡቲ እና ከህንድ መንግስታት ጋር በሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት ማጽደቂያ አዋጆችም ከጸደቁት መካከል ይገኙበታል።

የከፍተኛ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ፣  የማዕድን ግብይትን ለማስተዳደር የቀረበ አዋጅና የኮሚኒኬሽን አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ ባለፈው ሚያዚያ ወር ወደ ቋሚ ኮሚቴዎች የተመሩ መሆናቸው ተገልጿል።

በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያሉ ዋስትና መብት ረቂቅ አዋጅ፣ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅና የነዳጅና ነዳጅ ውጤቶች አቅርቦትና ስርጭት ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ማቋቋሚያ አዋጆችም ለቋሚ ኮሚቴ ከተመሩት መካከል ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም