በመካከለኛው አዋሽ በመስኖ ከሚለማው መሬት ግማሽ ያህሉ በአፈር ጨዋማነት ተጠቅቷል

147

ግንቦት 9/2011 በመካከለኛው አዋሽ በመስኖ ከሚለማው 16 ሺህ ሔክታር መሬት ውስጥ ግማሽ የሚሆነውን በአፈር ጨዋማነት የተጠቃና ተገቢው ምርት የማይገኝበት መሆኑን የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ገለፀ ።

በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ብሄራዊ የአፈር ምርምር ማስተባበሪያ በሆነው በወረር ግብርና ምርምር ማዕከል የአፈር ለምነትና ጤንነት ተመራማሪ አቶ አሸናፊ ወርቁ እንደገለፁት በመካከለኛው አዋሽ በባለሃብቶችና በከፊል አርሶ አደሮች በመስኖ ከሚለማው 16 ሺህ ሔክታር መሬት ውስጥ 46 በመቶው በአፈር ጨዋማነት የተጠቃ ነው ።

የችግሩ ዋናው መንስኤ ለውሃው አይከፈልም በሚል ግድየለሽነት ከመጠን በላይ ውሃ ለመስኖ ልማት መጠቀም መሆኑን የገለፁት ተመራማሪው “በተለይ መሬት ተከራይተው የሚያለሙ ባለሃብቶች በአንድና በሁለት ዓመት የተሻለ ምርት ለማግኘት እንጂ ስለመሬቱ ዘላቂ ደህንነት አይጨነቁም” ሲሉ ወቅሰዋል ።

የምርምር ማዕከሉ የአፈር ጨዋማነት የሚያስከትለውን የምርታማነት ማነስ ችግር ለመፍታት ያካሄዳቸው ምርምሮች ውጤታማ እየሆኑለት መምጣታቸውንም ተማራማሪው ገልፀዋል ።

“በአንድ በኩል የአፈር ጨዋማነትን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቆላ መስኖ ልማት የሰብል ዝርያዎችን በምርምር ማውጣትና የተመሰከረላቸው ዝርያዎችን ከውጪ በማስገባት በሌላ በኩል ደግሞ የተጠቃውን አፈር በማጠብ ፣ በማጠንፈፍ ፣ በጅብሰምና የተፈጥሮ ቅጠሎችን በማከም ወደ ምርታማነት እንዲመለስ እየተደረገ ነውም” ብለዋል ።

ማዕከሉ የአፈር ጨዋማነትን ተቋቁመው የተሻለ ምርት የሚሰጡ በምርምር ያወጣቸው አራት የሳር ፣ ሁለት የቅጠላቅጠል ፣ ሁለት የስንዴ ፣ ሶስት የጥጥና ሁለት የሩዝ ዝርያዎችን በአካባቢው ለሚገኙ ባለሃብቶችና ከፊል አርብቶ አደሮች እንዲደርሱ አድርጓል ።

በተጨማሪም የአፈር ጨዋማነት የሚቋቋሙ ገብስ ፣ ማሽላና ኪነዋ የመሳሰሉ ስድስት የሰብል ዝርያዎች ከውጪ በማስገባትና በማላመድ ለተጠቃሚው የማዳረስ ስራ እየተካሄደ መሆኑን አቶ አሸናፊ ተናግረዋል ።

በምርምር ማዕከሉ የመስኖ ልማት ተመራማሪ አቶ ጀማል መሀመድ በበኩላቸው አሁን በመስኖ ልማት ዘርፍ የሚታየው ቅጥ ያጣ የውሃ አጠቃቀም ነገ የግጭትና የድርቅ ምንጭ ሊሆን ስለሚችል በአግባቡ ጥቅም ላይ ሊውል እንደሚገባ አሳስበዋል ።

ከመጠን በላይ አሁን የምናባክነው ውሃ የእርሻ ማሳዎቻችን በጨዋማነት ተጠቅተው ከምርታማነት ውጭ እንዲሆኑና በውሃ እጥረት ምክንያት እርሰ በርሳችን እንድንጋጭ የሚያደርግ በመሆኑ ከወዲሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያዋጣ መክረዋል ።

“ውሃ በሒደት እያለቀ የሚሄድ ሀብት በመሆኑ ተለክቶና ተመጥኖ ጥቅም ላይ ማዋል” ይገባል ያሉት የዘርፉ ተመራማሪ የመስኖ ውሃን መጥኖ መጠቀምና የተረፈውን ውሃ ተመልሶ ወደ መጣበት ምንጭ እንዲገባ የሚያደርግ አሰራርን የማስተዋወቅ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

የወረር ምርምር ማዕከል በተለያዩ በመስኖ የሚለሙ የሰብል ዓይነቶች ላይ የውሃ ልኬት መጠን የሚወስን ምርምር ማድረጉን አቶ ጀማል ገልፀው ስንዴን በመስኖ ለማልማት በጥቁር አፈር በየ10 ቀኑ 100 ሚሊ ሜትር በአሸዋማ አፈር ደግሞ በየአምስት ቀኑ 75 ሚሊ ሜትር ውሃ ማጠጣት በቂ መሆኑን አስረድተዋል ።

“የጥጥ ልማት ለማካሄድ ደግሞ በየሁለት ሳምንቱ 75 ሚሊ ሜትር ውሃ ማጠጣት በቂ በመሆኑ አልሚዎች እንዲተገብሩት እየተሰራ ነው” ብለዋል ። 

በአፋር ክልል በወረር አካባቢ በግብርና ልማት የተሰማሩ ባለሃብት አቶ ደምለው ገበየሁ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የአፈር ጨዋማነት ልዩ ትኩረት አግኝቶ ካልተሰራበት በምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ የከፋ ይሆናል ።

ባለፈው ዓመት በ76 ሔክታር መሬት ላይ የዘሩት ጥጥ በአፈር ጨዋማነት ምክንያት መጥፋቱን ገልፀው የምርምር ማዕከሉ ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ ብለዋል ።

የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አበጀ መንገሻ እንዳሉት ውሃን ከሚጠቀሙበት በላይ በሚይዙና የተረፋቸውን መልሰው በማይለቁ ተቋማት ላይ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ ለመውሰድ በመዘጋጀቱ ጨዋማነትን በመቀነስ ረገድ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል የሚል ሃሳብ እንዳላቸው አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም