የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መካሄድ ይጀምራሉ

85

አዲስ አበባ  ግንቦት 9/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ደደቢት ከባህርዳር ከተማ በዝግ ስታዲየም ዛሬ ይጫወታሉ።

ጨዋታው የሚከናወነው በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት መሆኑንም የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል።

ጨዋታው በዝግ ስታዲየም እንዲካሄድ የሚደረገው የሚካሄደው በ23ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ ግብር ደደቢት እና ፋሲል ከነማ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ተከስቶ በነበረው የተመልካቾች ረብሻ ጨዋታው በመቋረጡ ነው።

ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስነ ስርአት ኮሚቴ ደደቢት ሁለት በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በዝግ ስታዲየም እንዲያደርግ ቅጣት ተላልፎበታል።

ደደቢት ከዛሬው ጨዋታ በተጨማሪ በቀጣይ በሜዳው የሚያደርገውን ጨዋታም ያለ ተመልካች በዝግ ስታዲየም የሚያከናውን ይሆናል።

የ25ኛው መርሃ ግብር ቀጥሎ ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 10 ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በክልል ከተሞች ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ ከወላይታ ድቻ ፤ደቡብ ፖሊስ ከስሑል ሽረ በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ኢትዮጵያ ቡና ሲዳማ ቡናን ያስተናግዳል።

በክልል ከተሞች ሶስት ጨዋታዎች ሲከናሄዱ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከሀዋሳ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከአዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ከጅማ አባ ጅፋር በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ።

በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም ነገ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ፤ፌዴራል ፖሊስ ከፕሪሚየር ሊጉ መሪ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ጋር ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በክልል ከተሞች ጎንደር ላይ ጎንደር ከተማ ከመከላከያ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ፤ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜ ከቡታጅራ ከተማ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ይጫወታሉ።

ከነገ በስቲያ መቐለ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከድሬዳዋ ከተማ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል።

በወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታዎችም ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲዮም ሙገር ሲሚንቶ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ ከአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ በተመሳሳይ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ባህርዳር ላይ ጣና ባህርዳር ከመከለካያ ተስተካካይ ጨዋታቸውን ማድረግ የነበረባቸው ቢሆንም መከላከያ በተጫዋቾች ጉዳት እና በዝግጅት ማነስ ምክንያት ጨዋታው ለሌላ ጊዜ ይራዘምልኝ የሚል ጥያቄ በማቅረቡ ጨዋታው ለሌላ ጊዜ መራዘሙን ከኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ተስተካካይ ጨዋታዎቹ የፕሪሚየር ሊጉ ስምንተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሲሆኑ ሙገር ሲሚንቶና ወላይታ ድቻ በአፍሪካ ቮሊቦል ክለቦች ውድድር ተሳትፎ ላይ የነበሩበት ወቅት መሆኑና የመከላከያና የጣና ባህርዳር ጨዋታ ደግሞ ጣና ባህርዳር በነበረበት የገንዘብ ችግር ምክንያት ጨዋታዎቹ መራዘማቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም