የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ክፍያ ብንፈጽምም ለሦስት ዓመታት ምላሽ አላገኘንም.... በወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪዎች

63
ሶዶ  ግንቦት 29/2010 በወላይታ ሶዶ ከተማ ድል በትግል ቀበሌ የሚኖሩ ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ተገቢውን ክፍያ ብንፈጽምም ላለፉት ሦስት ዓመታት ምላሽ አላገኘንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገለጹ፡፡ ከተማ አስተዳደሩም በበኩሉ  “ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለትራንስፎርመር ግዢ ከ300 ሺህ ብር በላይ ክፍያ ፈጽሜያለሁ ችግሩ የኔ አይደለም” ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎትም የነዋሪዎችም ሆነ የከተማ አስተዳደሩን ጥያቄዎች እስከበጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን አስታዉቋል፡፡ በወላይታ ሶዶ ከተማ ድል በትግል ቀበሌ ነዋሪዎች እንዳሉት በ2007 ዓ.ም እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ መብራት እንዲገባላቸው ሰላሳ በሰባ በሚባለው የማህበረሰብ የልማት አሰራር በነፍስ ወከፍ ከ500 ብር በላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ይሁንና እስካሁን ድረስ ለጥያቄያቸው ምላሽ ባለማግኘታቸው ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ለኢዜአ ገልጸዋል። በቀበሌው የቆንቶ መንደር ነዋሪና የመንደሩ ሊቀመንበር አቶ ዘካሪያስ ሹኬ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በመንደሩ እየኖሩ መሆኑንና ከረጅም ዓመታት ጥያቄ በኋላ በ2007 ዓ.ም መብራት ይገባላችኋል በሚል እያንዳንዱ የመንደሩ ነዋሪ ብር 500 ክፍያ መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡ ዛሬም ከሦስት ዓመት በኋላ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አለማግኘታቸውን የተናገሩት አቶ ዘካሪያስ፣ ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ ከሚርቅ መንደር የኤሌክትሪክ ኃይል በገመድ ከግለሰብ ስበው ለማምጣት ጥረት ቢያደርጉም የኤሌክትሪክ ሽቦው በመጠላለፍ ተደጋጋሚ አደጋ መከሰቱን ጠቁመዋል፡፡ “ለችግራችን መፍትሄ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም የከፈልነው ገንዘብ እንኳ የት እንደደረሰ ምላሽ የሚሰጥ አካል በማጣታችን ቅሬታ አድሮብናል” ብለዋል፡፡ ሌላኛው የመንደሩ ነዋሪ ወይዘሮ መክብብ ጆባ በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል ባለማግኘታቸው ለአንድ አምፖል በወር እስከ 30 ብር ከፍለው ከሌላ መንደር ኃይል ለመሳብ መገደዳቸውንና በዚህም ለተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ከግለሰብ በገመድ ስበው ያስመጡት የኤሌክትሪክ ኃይል ከሩቅ አካባቢ የሚሳብ በመሆኑ በተደጋጋሚ የኃይል እጥረት እንደሚያጋማቸውና በእዚህም ልጆቻቸው ለጥናት ኩራዝ ሲጠቀሙ ለአይን ሕመም እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የወላይታ ሶዶ ከተማ ካንቲባ አቶ ጸጋዬ ኤካ በከተማው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር በሰፊው እንደሚስተዋልና በእዚህም ነዋሪው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አድርጎ በተደጋጋሚ እያነሳው መሆኑን አስረድተዋል። በተለይ በድል በትግል ቀበሌ ባሉ ሦስት መንደሮች ያለው የኃይል ችግር እንዲፈታ ከተማ አስተዳደሩ ለትራንስፎርመር መግዣ የሚሆን 300 ሺህ ብር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት  ክፍያ በ2008 ዓ.ም መፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡ በቀበሌው ካሉ ሦስቱ መንደሮች የቆንቶ መንደር ነዋሪዎች ያዋጡት ገንዘብም በእዚህ ክፍያ የተካተተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለነዋሪዎች ቅሬታ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ ኤልትሪክ ኃይልን በተደጋጋሚ  ቢጠይቁም ምላሽ ማጣታቸውን የገለጹት አቶ ጸጋዬ፣ ለክልሉ መንግስት ጉዳዩን በማሳወቅ መልስ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ደቡብ ሪጅን የወላይታ ሶዶ ዲስትሪክት የቴክኒክ ክፍል ኃላፊ አቶ አለማየሁ አዛቼ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ እንዳሉት ለቆንቶ ሆርባብቾና አውራ ጎዳና መንደሮች የሚሆን ትራንስፎርመር ግዢ ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ ከደቡብ ሪጅን ትራንስፎርመርና ሌሎች አስፈላጊ ግብአቶች ፈጥነው አለመምጣት፣ የደንበኞችን ፋይል ወደ ዲጂታል ሲስተም የመቀየር ሥራና በሌሎች ደራሽ ሥራዎች መጠመድ ለነዋሪዎቹ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት አለማስቻላቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም በከተማዋ ከሚስተዋሉ የልማት ሥራዎች ጋር ተያይዞ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መብዛታቸው ምላሹ እንዲጓተት ማድረጉን አስረድተዋል። በተለይ በሁለቱ መንደሮች ያለውን የነዋሪዎች ጥያቄ እስከበጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ለመመለስ አስፈላጊ ግብአቶችን ለማግኘት ከደቡብ ሪጅን ጋር መነጋገራቸውንና ግብአቱ እንደደረሰ ፈጥነው ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸዋል። በሶዶ ከተማ የሚስተዋለውን የመብራት ተደራሽነትና መቆራረጥን ለማስቀረት የሚያስችሉ ግብአቶችን የማሟላት ተግባርም በዲስትሪክቱ ትኩረት እንደተሰጠው አመልክተዋል። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደቡብ ሪጅን ሪቴል ቢዝነስ ኃላፊ አቶ ታደሰ አመርጋ በበኩላቸው የነዋሪዎቹ ቅሬታ አግባብ መሆኑን ገልጸው በከተማዋ ለሰፋፊ የልማት ሥራዎች ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱ የነዋሪዎቹ ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ እንዲዘገይ ማድረጉን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ከወላይታ ሶዶ ዲስትሪክት የቀረቡ የኃይል አቅርቦት ጥያቄዎችን ለመመለስ አስፈላጊ ግብአቶች ተገዝተው ወደ ዲስትሪክቱ የማጓጓዝ ሥራ መጀመሩንና በቀጣይ የነዋሪዎቹ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የሚደረግ መሆኑን አስታውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም