በድሬዳዋ አስተዳደር ለ17ሺህ ሰዎች የሥራ እድል መፈጠሩን ምክትል ከንቲባው ገለጹ

243

ድሬዳዋ ግንቦት 8 / 2011በድሬዳዋ አስተዳደር ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ17ሺህ በላይ ለሚበልጡ ዜጎች  የሥራ እድል  መፈጠሩን ምክትል ከንቲባ ማሃዲ ጊሬ ገለጹ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት 41ኛው መደበኛ ጉባዔውን ዛሬ ጀምሯል፡፡

ከንቲባ መሃዲ ጊሬ በጉባኤው ላይ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳመለከቱት በአስተዳደሩ ሥራ አጥ ለነበሩት ወገኖች  የሥራ ባለቤት የሆኑት በሥራ ዕድል ፈጠራና በምግብ ዋስትና መርሃ ግብሮች ነው።

 በዚህም ከ9ሺህ300 ዜጎች ቋሚና ቀሪዎቹ ደግሞ ጊዜያዊ ሥራ እንደተፈጠረላቸው አስታውቀዋል።

ሥራ ከተፈጠረላቸው ሰዎች ውስጥ 42 በመቶ ያህሉ ሴቶች መሆናቸውንም አቶ መሃዲ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም በአስተዳደሩ የተፈጠረው ሥራ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ከመፍታት አኳያ  በቂ እንዳልሆነም አምነዋል፡፡

በተጨማሪም ከ23 ሺ 500 በላይ ነዋሪዎች በደረቅ ቆሻሻ ማሰባሰቢያና ማስወገድ እንዲሁም በተፋሰስ ሥራ ተሰማርተው ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ለ306 ኢንተርፕራይዞች ከ87ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፈጠሩንም   ምክትል ከንቲባው ገልጸዋል፡፡

ለኢንተርፕራዞቹ 89 ሚሊዮን ብር ብድር የተሰጠ ሲሆን፣ 2ነጥብ2 ሚሊዮን ብር ውዝፍ ብድር መመለሱን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም 1ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች ፈቃድ ወስደው እንቅስቃሴ መጀመራቸውን አቶ መሃዲ  በሪፖርታቸው አመልክተዋል፡፡

የህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት የተተገበሩት 189 ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ጉድለት እንደታየባቸው ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል፡፡

ህዝቡን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመፍታት የተተገበሩት 189 ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም ጉድለት እንደታየባቸው ምክትል ከንቲባው አመልክተዋል፡፡

የአስተዳደሩ ምክር ቤት የማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መሐመድ አብዱላሂ በትምህርትና በጤናው ዘርፎች የተከናወኑት ተግባራት በቂ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአስተዳደሩ ካቢኔ በሪፖርት በሚቀርብለት ሳይሆን፤ በተጨባጭ ከሚታየው ጋር በማጣጣም በየደረጃው ተጠያቂነትን  እንዲያሰፍን አሳስበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባል አቶ ታጁዲን ዑመር በበኩላቸው የገጠር ወጣቶችሥራ ፈጠራ ሊተኮርበት እንደሚገባ  አስገንዝበዋል፡፡

በመስኖና የመሠረተ ልማት ችግሮችን ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት  አለመታየታቸውንም ተናግረዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በሪፖርቱ ላይ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ነገ  ምላሽ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ምክር ቤቱ በነገ ውሎው የአስተዳደሩ የውዝፍ ሥራዎችና የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤትን የሥራ ዘመን ቆይታ ያራዝማል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪ ሹመቶችን እንደሚሰጥ ለጉባዔው የተያዘው መርሐ ግብር አመልክቷል፡፡