ተቋማቱ በፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ተጠየቀ

71

አዳማግንቦት 8 /2011 የመንግሥትና የግል የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማት በፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ተጠየቀ።

በኦሮሚያ ክልል ከ70 በላይ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች የተሳተፉበት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ዐውደ ርዕይ በአዳማ ከተማ ዛሬ ተከፍቷል።

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ተቋማቱ በቴክኖሎጂ መቅዳትና ማላመድ ዙሪያ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን ቴክኖሎጂን ማስፋፋት ይጠበቅባቸዋል።

በዚህም ቴክኖሎጂውን ለኢንተርፕራይዞች፣ አንቀሳቃሾችና አርሶ አደሮች ተደራሽ በማድረግ ተወዳዳሪ ማድረግ ጥራትና ተወዳዳሪነት ያላቸው ምርትና አገልግሎቶችን ለአገር ውስጥና ለውጭ ለማቅረብ  እንደሚያስችል ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂ የበለፀጉ ተቋማትን ለመፍጠርም ሰልጣኞች፣አሰልጣኞችና ኢንተርፕራይዞች በቴክኖሎጂ ፣ክህሎትና ምርምር ላይ በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።

የኦሮሚያ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤባ ገርባ እንደገለጹት ተቋማቱ ውጤት ተኮር ሥርዓተ ትምህርትና ስትራቴጂ በመከተል የፈጠራና የቴክኖሎጂ ሽግግር እያመጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ዘንድሮ ከ800 በላይ የሚሆኑ የግብርና መካናይዜሽን በተለይም የማጨጃ፣ የእርሻና የመውቂያ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶችን ለኢንተርፕራይዞችና አንቀሳቃሾች ተደራሽ ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

ዐውደ ርዕዩ አገሪቷ የጀመረችውን የኢኮኖሚ ሪፎርም በቴክኖሎጂ ፣በክህሎት፣ በጥናትና ምርምር በመደገፍ በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ለመተካት ልምድ እንደሚቀስሙበት ገልጸዋል።

በጥቃቅንና አነስተኛ የምርት ጥራትና አገልግሎትን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎችን ለመፈብረክ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ለፈጠራ ሥራዎች መመደቡን የተናገሩት ደግሞ የአዳማ ከተማ ከንቲባ አቶ መስፍን አሰፋ ናቸው።

በዐውደ ርዕዩ ከተሳተፉት መካከል የጅማ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ አሰልጣኝ አቶ አፈወርቂ ጽጌ ኮሌጁ በግብርና ፣ በወተት፣በዶሮ እርባታና በአገልግሎት በምርምር ያወጣውን ቴክኖሎጂ አቅርበዋል ብለዋል።

ከቀረቡት ቴክኖሎጂዎች መካከል የበቆሎ መፈልፈያ ፣ የጤፍ መውቂያ፣የሽንኩርትና የቡና መፍጫ እንዲሁም የመኖ ማዘጋጃና የወተት መናጫ ይገኙበታል።

ለሦስት ቀናት በሚቆየው ዐውደ ርዕይ ላይ ለፈጠራ ባለቤቶችና የተሻለ አፈፃፀም ላላቸው ተቋማት ዕውቅና እንደሚሰጥ ከወጣው መርሐ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም