በ270 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለሚከናወነው የመቐለ ከተማ ውሃ ፕሮጀክት ዝግጅት ተጠናቀቀ

433

ግንቦት 8/2011 የመቐለ ከተማ በ270 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለሚከናወነው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ዝግጅቱ መጠናቀቁን የትግራይ ክልል ውሃ ሃብት ቢሮ አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ የከተማዋን የውሃ እቅርቦት 90 በመቶ ያደርሰዋል ተብሎም ይጠበቃል።

የቢሮው ኃላፊ ኢንጀሂነር ቴዎድሮስ ገብረእግዚአብሄር ዛሬ እንደተናገሩት በሦስት ዓመታት ውስጥ የሚጠናቀቀውን ፕሮጀክት ከቻይና መንግሥት በተገኘ ብድር ይሆናል።

ከከተማው በስተምዕራብ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኘው ገረብ ግባ ተብሎ በሚጠራው ወንዝ ላይ ለሚገነባው ፕሮጀክት ከባድ ማሽነሪዎች፤ባለሙያዎችና ሌሎች ግብአቶችን መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል።

ግድቡ 362 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ዉሃ የሚይዝ ሲሆን፣1ነጥብ 3 ኪሎሜትር ስኩየር ስፋትና 84 ሜትር ከፍታ ይኖረዋል ብለዋል።

እንዲሁም ለ20 ዓመታት አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር የከተማዋን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትን አሁን ካለበት 53 በመቶ ወደ 90በመቶ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል።

ግድቡ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ከመስጠት ባለፈ ለኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል።

የግድብ ግንባታ ስራው ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የአከባቢው አርሶ አደሮችና ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

በግንባታው ምክንያት የእርሻ መሬታቸው ለሚወሰድባቸው የእንደርታ፤የክልተ ኣውላዕሎ እና የደጉዓ ተምቤን ወረዳ አርሶ አደሮች የመሬት ካሳ ከ1ነጥብ7 ቢልዮን ብር በላይ ለመስጠት በትግራይ ክልል መንግስት የፀደቀ መሆኑ አስታውቋል።