ስኳር ድንች ለህፃናት የበለጸገ ቫይታሚን “ኤ” ይዘት ያለው ንጥረ ነገር ለማቅረብ እንደሚያስችል ተጠቆመ

240

ግንቦት 8/2011ስኳር ድንች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ለሚጠቁ ህፃናት የበለጸገ ቫይታሚን “ኤ” ይዘት ያለው ንጥረ ነገር ለማቅረብ እንደሚያስችል ተጠቆመ።

ምርቱ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት በስፋት እንዲመረት እየተደረገ መሆኑም ተመልክቷል።

የስኳር ድንች ምርትን በአፍሪካ አገራት ለማስፋፋት እየተደረገ ባለው ጥረት፣ ያሉትን መልካም ተሞክሮዎችና ተግዳረቶችን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ የውይይት መድረክ በመቀሌ ከተማ ተካሄዷል።

በውይይቱ ላይ ስኳር ድንች የሚመረትባቸው 14 የአፍሪካ አገራትን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ የስኳር ድንች ምርምር ማዕከልና ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት በዘርፉ የተሰማሩ ከፍተኛ ምሁራን ተሳትፏል።

በዓለም አቀፍ የስኳር ድንች ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪና በአፍሪካ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶክተር ጃን ሎው እንደገለጹት፣ ምርቱ በአነስተኛ ውሃ የሚበቅል  በመሆኑ በዝናብ እጥረት በሚጠቁ አገራት ተመራጭ ነው።

“ምርቱን በአርሶአደሮች ማሳ ላይ ማስፋፋት የተፈለገው በቫይታሚን “ኤ” እና በኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮች የተሞላ በመሆኑ ነው” ያሉት አስተባባሪዋ፣ በምግብ እጥረት ምክንያት በህጻናት ላይ የሚከሰተውን የመቀንጨር ችግር ለመከላከልና ህጻናቱን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ከቅጠሉና ከግንዱ ጀምሮ ለምግብነት እንደሚያገለግልና ከሌሎች ምርቶች ጋር ሲነፃፀርም በአነስተኛ ማሳ የተሻለ የምርት መጠንን የሚያስገኝ በመሆኑ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዋነኛ ተመራጭ መሆኑንም ገልጸዋል።

ተሳታፊዎቹ በአፍሪካ አገራት በዘርፉ ያለውን ተሞክሮ በማንሳት ልምድ የተለዋወጡ ሲሆን፣ ምርቱን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።

በተጨማሪም አርሶ አደሮች ተግባራዊ ልምምድ እንዲያደርጉ ማድረግ፣ በቅርበት ሙያዊ ድጋፍ የሚያገኙበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠርና አዳዲስ የስኳር ድንች ዝርያዎችን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ላይ አንስተዋል።

በትግራይ የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር በየነ ድምፁ በበኩላቸው፣ “ውይይቱ ጥራቱን የጠበቀ የስኳር ድንች ዘር ለማቅረብ ሁኔታዎችን ለማመቻቸትና በሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል” ብለዋል።

በትግራይ ክልል በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ከ15 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በስኳር ድንች ልማቱ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አመልክተዋል። 

በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተሻለ የስኳር ድንች ዘር አቅርቦት መኖሩንም ጠቁመዋል።

እንደ ዶክተር በየነ ገለጻ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የስኳር ድንች ዘርን ለማባዛትና ህብረተሰቡ ከሚጠቀምባቸው የምግብ አይነቶች ጋር አብሮ እንዲጠቀም ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን በእንደርታ ወረዳ በጨለቆት ቀበሌ የሚኖሩት አርሶአደር ካልአዩ ሕሉፍ በበኩላቸው፣ ስኳር ድንችን ማምረት ከጀመሩ አምስት ዓመት እንደሞላቸው ተናግረዋል።

ሩብ ጥማድ የሚሆን ማሳቸውን በስኳር ድንች በማልማት ቤተሰቦቻቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደቻሉም ገልጸዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ከምርቱ ሽያጭ ባገኙት ገቢም ከአምስት በላይ የቤት እንስሳት ባለቤት ለመሆን መቻላቸውን ነው የተናገሩት።

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ሙሉ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ስኳር ድንች በጓሮ አትክልት መልማት መቻሉ እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎች ሴቶችም በልማቱ እንዲሳተፉ አድርጓል።

ከሌሎች የእህል አይነቶች ጋር በመቀላቀል ለምግብነት በማዋላቸው ራሳቸውና ቤተሰቦቻቸውን በተሻለ ጤንነት ለመጠበቅ መቻላቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም