በመቱ ዩኒቨርስቲ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

74

 ግንቦት  8/201 1 በመቱ ዩኒቨርስቲ የሚስተዋለው የአግልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር   ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ዩኒቨርስቲው ገለጸ።

የተቋሙ ሰራተኞች በአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈታላቸው ሰሞኑን መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው ዩኒቨርስቲው ዛሬ  መግለጫ    የሰጠው፡፡

የትራንስፖርት፣ የኢንተር ኔት እና የፋይናንስ አሰራር  ችግሮች  እንዲፈቱላቸው ሰራተኞቹ ከጠየቋቸው መካከል ይገኙበታል።

የዩኒቨርስቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ዶክተር ለታ ዴሬሳ  በመግለጫቸው እንዳሉት ሰራተኞቹ ያቀረቡት ጥያቄና ያነሱት ቅሬታ ትክክል ነው።

ችግሮቹን በተቻለ መጠን በፍጥነት ለመፍታት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በኢንተርኔት ችግር የተነሳ የትምህርት ክፍሎች፣ ቤተ መጻህፍትና ቤተ ሙከራዎች ስራቸውን በአግባቡ መስራት እንዳልቻሉ ጠቁመው ችግሩን ለመፍታትም በ127 ሚሊዮን ብር በአንድ የቻይና ተቋም የመስመር ዝርጋታ ስራ እየተፋጠነ እንደሆነ ተናግረዋል።

በፋይናንስ ዘርፍና ሌሎች የአስተዳደር መስኮች የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታትም በየኮሌጆችና በየፋከልቲዎች ለማደራጀት አዲስ መዋቅር ተሰርቶ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በመጪው የትምህርት ዘመንም መስፈርቱን ባሟሉ ኮሌጆችና ፋከልቲዎች ተግባራዊ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በትራንስፖርት አቅርቦት በኩል የተነሱ ችግሮችም ዩኒቨርስቲው በቂ ተሽከርካሪዎች ስለሌሉት እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ለታ  ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ለማስተካከል እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም