የኢትዮጵያና አሜሪካ የኢኮኖሚ አጋርነት ፎረም እየተካሄደ ነው

75

ግንቦት 8/2011 የኢትዮጵያና አሜሪካ የኢኮኖሚ አጋርነት ፎረም ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ዛሬ መካሄድ ጀመረ።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተካሄደ ያለው ፎረም ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በፎረሙ ላይም በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ገለፃ ይደረጋል።

በፎረሙ ላይ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ቲቦር ናሽ፣ አምባሳደር ፍፁም አረጋን እና ዶክተር አርከበ እቁባይን ጨምሮ የተለያዩ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያ የንግድ ማህበረሰብ መሪዎች በጎ አድራጊ ግለሰቦች እየተሳተፉ ነው።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍፁም እና ዶክተር አርከበ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያለውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ለውጥን በተመለከተ ለፎረሙ ተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።

አምባሳደር ፍጹም በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድሎች፣ እየተወሰዱ ስላሉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ላይ አመርቂ ምክክር መደረጉን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።ራቱ

ጉባዔው በነገው ውሎው በፋይናንስ አቅርቦት፣ በመሰረተ ልማት ግንባታ፣ በቴሌኮም፣ በኃይል አቅርቦትና የትራንስፖር ዘርፍ እና ግብርና ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በሚኖራቸው ሚና ላይ ይመክራል።

የኢትዮጵያና አሜሪካ የኢኮኖሚ አጋርነት ፎረም በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማሳደግ በማለም ነው የተዘጋጀው።

ከዚህ ባለፈም ለአሜሪካ የንግድ ሰዎች በኢትዮጵያ ያሉትን የተለያዩ የንግድ ዕድሎችን በማሳወቅ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያስችል ነው ተብሏል።

ይህም በአገራቱ መካከል ያለውን የንግድ፣ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑ ነው ተገልጿል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለውን የኢኮኖሚና የንግድና ሁለንተናዊ ለውጥ ለማበረታታት እንደሚያስችል ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም