በአደአ ወረዳ የተቀናጀ የዓሳ ግብርና መንደር ተቋቋመ

116

ግንቦት 8/2011 በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን አደአ ወረዳ አርሶ አደሮች በየቤታቸው አሳ የሚያመርቱበት መንደር ተቋቋመ ።

በክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ባቱ ዓሳና ሌሎች የውሃ ውስጥ ህይወት ምርምር ማዕከል ከፍተኛ ተመራማሪና ሃላፊ ዶክተር ለማ አበራ እንደገለፁት በወረዳው ጎዲኖ ጂቱ ቀበሌ የተቋቋመው መንደር ለአርሶ አደሮች ድርብ ጥቅም የሚያስገኝ ነው።

በተቀናጀ የዓሳ ግብርና መንደሩ ላይ አንድ አርሶ አደር በተቀናጀ መልኩ በመኖሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ የዶሮ እርባታ ፣ የእንስሳት መኖ ዝግጅት፣ የከብት ማድለብ ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና የዓሳ እርባታ ያካሔዳል ።

ከምርምር ማእከሉ የወጣው አዲሱ ቴክኖሎጂ ባለፈው ዓመት በአንድ ሞዴል አርሶ አደር ተሞክሮ ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱ ዘንድሮ በመንደር ደረጃ የማስፋፋት ስራ እየተካሄደ  መሆኑንም ዶክተር ለማ ተናግረዋል ።

እያንዳንዱ አርሶ አደር የዓሳ እርባታውን የሚያከናውነው ስምንት ሜትር ስፋትና  10 ሜትር ርዝመት ባለው ኩሬ ውስጥ ከ500 በላይ የዓሳ ጫጩቶችን በመጨመር ነው ።

ከኩሬው ጋር ተያይዞ የሚከናወነው የዶሮ እርባታ ደግሞ አርሶ አደሩን በእንቁላል  ተጠቃሚ ከማድረጉ ባሻገር የዶሮዎቹ ኩስ ወደ ውሃው እንዲገባ በማድረግ ዓሳዎቹ ያለ ተጨማሪ ምግብ እንዲቀለቡት ይደረጋል ።

ኩሬው ውሃ የሚያገኘው ለመስኖ ልማት ከተዘረጋው ቦይ ጠልፎ በማስገባት ሲሆን በኩሬው ዙሪያ ላይ የተሻሻሉ የመኖ ዝርያዎችን በእርጥበት በማምረት ለእንስሳት ማድለብ ጥቅም ይውላል ።

“አርሶ አደሮቹ የኩሬውን ውሃ መጥነው በመልቀቅ ለአትክልትና ፍራፍሬ ልማት  እንደሚጠቀሙበት ተመራማሪው ገልፀው ውሃው በቂ የዶሮ ኩስ፣ ውሃ አቅላሚ ( አልጌ ) ያለውና ዳፕና ዩሪያ ማዳበሪያዎችን የሚተካ ንጥረ ነገር አካትቶ የያዘ በመሆኑ ኦርጋኒክ አትክልትና ፍራፍሬ ለማምረት ይጠቅማል” ብለዋል ።

ይኽው የተቀናጀ የዓሳ ግብርና መንደር የምርምር ማዕከሉ በበላይነት በግብርና እድገት ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ የሚያካሔደው ሲሆን ከአርሶ አደሩ እየቀረበ ካለው ጥያቄ አንፃር በብዛት ተደራሽ ማድረግ እንዳልተቻለ ተናግረዋል ።

ፕሮጀክቱ ለእያንዳንዱ አርሶ አደር 30 ዶሮዎችና 500 የዓሳ ጫጩቶች ከመስጠት ባሻገር የቅርብ ሙያዊ እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ዶክተር ለማ ገልፀው ከአሁን በኋላ ግን በሞዴልና ተመራማሪ አርሶ አደሮች እየተመራ እንዲስፋፋ እቅድ ወጥቶ ስልጠና መሰጠቱን አስረድተዋል።

ፕሮጀክቱን በሙከራ ደረጃ ተግብረው ውጤታማ የሆኑት ሞዴል አርሶ አደር አማረ አስራት በሰጡት አስተያየት ያመረቱትን ዓሳና እንቁላል በመሸጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ 30 ሺህ ብር ገቢ አግኝተዋል ።

ለገበያ የደረሰ አትክልክልት በብዛት እንዳላቸው ገልፀው ማንጎ ፣ ፓፓያ ፣ ቡና ፣ሸንኮራና የእንስሳት መኖ በተቀናጀ መልኩ እያመረቱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በአሁኑ ወቅት ቆሮሶ ፣ አምባዛና ዱቤ የተባሉ የዓሳ ዝርያዎች አጥምደው እየተጠቀሙ ሲሆን ከቤት ፍጆታ በዘለለ አንዱን ዓሳ በ20 ብር ሒሳብ በመሸጥ ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል ።

የሞዴል አርሶ አደሩ መልካም ተሞክሮ በመጋራት ወደ ተቀናጀ የዓሳ ግብርና መንደር  የተቀላቀሉት አርሶ አደር ታደሰ በቀለ በበኩላቸው 750 የዓሳ ጫጩቶች ወደ ኩሬአቸው በማስገባት ምርቱ እስኪደርስላቸው ድረስ እየተጠባበቁ መሆናቸው ገልፀዋል ።

ከዶሮዎቹ የተገኘውን እንቁላል ለገበያ በማቅረብ የተሻለ ገቢ ማግኘት መጀመራቸውንም አስረድተዋል።

አቶ ሲሳይ አሰፋ የተባሉ የጎዲኖ ጂቱ ሞዴል አርሶ አደር በበኩላቸው 551 የዓሳ ጫጩቶች ወደ ኩሬ በማስገባት ለመብል መድረሳቸውንና በፍጥነትም እየተባዙ መሆናቸው  ገልጸዋል።

ከዶሮዎቹ የሚያገኙት እንቁላል አንዱን በ3ብር ከ50 ሳንቲም ሂሳብ ለገበያ በማቅረብ  ተጠቃሚ መሆናቸውን በመግለፅ ሌሎች አርሶ አደሮችም የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

በተቀናጀው የዓሳ ግብርና መንደር ውሱን አርሶ አደሮች የምርቱ ተጠቃሚዎች መሆን ሲጀምሩ ከ30 የሚበልጡ አርሶ አደሮች ወደ ስራ ለመግባት ተመዝግበው የምርምር ማዕከሉን ድጋፍ ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም