በጎባ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ ሲሆኑ ጋሰራዎቹ ሁኔታዎች አልተመቻቸልንም አሉ

59

ጎባ ግንቦት 8/2011 በባሌ ዞን ጎባ ወረዳ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተሰማሩ ወጣቶች ውጤታማ መሆናቸውን ሲገልጹ፣የጋሰራ ወረዳ ወጣቶች የብድርና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ስላልተደረገላቸው ተጠቃሚ አልሆንም እያሉ ናቸው

የዞኑ የኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት በበኩሉ ዘንድሮ 28 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችን ወደ ሥራ ቢያስገባም፤የብድር አመላለስ  ሥራውን እያደናቀፈበት መሆኑን ይገልጻል፡፡

በጎባ ወረዳ ወጣቶች መካከል ወሰንዬለህ ንጋቱ እንደገለጸው ከኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም በብድር በወሰዱት 45ሺህ ብር የመነሻ ካፒታል ከሌሎች አምስት ጓደኞቹ ጋር በብሎኬት ምርት በመሰማራት አንድ ሚሊዮን ብር  የሚጠጋ ካፒታል እንዳፈሩ ተናግሯል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ባደረጉት እንቅስቃሴ ለ11 ሰዎች ሥራ መፍጠራቸውንም ገልጿ።

መንግሥት ባመቻቸላቸው ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ በመጠቀም በዶሮ እርባታ መስክ በመሰማራት ከቤተሰብ ጥገኝነት እንደተላቀቁና ለሌሎች ወጣቶችም ጊዜያዊ ሥራ በመፍጠራችን ደስተኞች ነን ሲል የተናገረው ደግሞ ሌላው የብድሩ ተጠቃሚ ወጣት አቤል ሙሉጌታ ነው፡፡

በአካባቢያቸው ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸውም ጠይቋል።

ብድራቸውን በወቅቱ በመክፈል ኃላፊነታችንን እየተወጣን እንገኛለን ብሏል፡፡

በሌላ በኩል የብድርና የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻሉ የጋሰራ ወረዳ ወጣቶች ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

በወረዳው ወጣቶች መካከል ሐሰን ኢድሪስ በሰጠው አስተያየት ከአንድ ዓመት በፊት ከሌሎች አምስት ጓደኞቹ ጋር በመሆን መስፈርት አሟልተው ቢደራጁም፤ የብድር አገልግሎት ባለመግኘታቸው ሥራ መጀመር እንዳልቻሉ ተናግሯል፡፡

”ችግሩን በማስመልከት ከወረዳ እስከ ዞን ላሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ብናሳውቅም እስካሁን መፍትሄ ባለማግኘታችን ከቤተሰብ ጥገኝነት መላቀቅ አልቻልንም” ብሏል፡፡

ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ ወጣት መንግስቱ መኮንን በበኩሉ ባለፈው ዓመት ከአራት ጓደኞቹ ጋር በመሆን ተደራጅተው በእንስሳት ማድለብና በወተት ላሞች እርባታ ሥራ ለመሰማራት የሚያስፈልጋቸውን መስፈርት አሟልተው ጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ጥያቄ እንዳቀረቡ ያስታውሳል።

“በመስፈርቱ መሰረት የሥራ ዕቅድ አዘጋጅተን ብድሩን ለማግኘት በቅድመ ሁኔታነት የሚጠበቅብንን 10 በመቶ ቆጥበናል” ያለው ወጣት አስቻለው  አበራ ብድሩንም ሆነ ለእርባታ የሚሆነውን ቦታ ባለማግኘታቸው ወደ ሥራ ሳይገቡ መቅረታቸውን ገልጿል።

ከብድር እጦትና ከመስሪያ ቦታ ችግር የተነሳ ከቤተሰብ ጥገኝነት ስላልተላቀቁ መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም የባሌ ዞን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደፎ ኡመሮ በሰጡት ምላሽ ከብድር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ወጣቶቹ የሚያነሱት ቅሬታ ትክክል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 

ችግሩ የተከሰተው ተቋሙ ባለፉት ዓመታት ለደንበኞቹ ያበደረው ተዘዋዋሪ  ፈንድ በወቅቱ ባለመመለሱ በሚፈለገው ደረጃ ብድሩን ለማሰራጨት እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ከአንድ ሺህ በሚበልጡ ማህበራት ሥር ለተደራጁ ማህበራት ከተሰጠው  30 ሚሊዮን ብር ብድር ውስጥ እስካሁን  የተመለሰው 12 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑን በማሳየነት አቅርበዋል፡፡

ብድሩ በወቅቱ አለመመለሱ የተቋሙን የማበደር አቅም ከመፈታተኑም በሻገር፤ ብድር የሚፈልጉ ወጣቶች  ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያስከተለ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ የኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጫልችሳ ዘውዴ እንደገለጹት ባለፉት ዘጠኝ ወራት 28 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶችን በጊዜያዊና ቋሚነት ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡  

ወደ ግብርና ሥራ የገቡ ወጣቶች ያለባቸውን የመነሻ ካፒታል እጥረት ለመፍታት 12 ሚሊዮን ብር ብድርና አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሄክታር መሬት መመቻቸቱንም ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት 49ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ቢታቀድም፤ በብድር አመላለስ ላይ እየታየ ባለው ክፍተት ዕቅዱን ተፈጻሚ ለማድረግ ችግር መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ወጣቶችን ወደ ስራ በማስገባትና በብድር አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል የዞኑ የኢንተርፕራይዞች ምክር ቤት ሰሞኑን ተቀምጦ ስራዎችን ከገመገመ በኋላ ቀሪ ስራዎችን በቀሩት ጊዜያት ውስጥ ለማጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጦ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

እንዲሁም ከተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ ጋር ተያይዞ ወጣቶቹ የሚያነሱትን ቅሬታ በአዲሱ ዓመት እቅድ ውስጥ በማስገባት በተጠና መልኩ ለመመለስ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑንም አመልክቷል፡፡

በዞኑ 18 ወረዳዎች ወጣቶቹ በዋናነት በግብርና፣ በዶሮ እርባታ፣ በእንጨትና ብረታ ብረት ሥራ፣ በእንሰሳት ንግድና ማድለብ ዘርፎች የተሰማሩ ሲሆን፣በለፉት ሁለት ዓመታት ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰራጨቱን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም