የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ድጋፍ አቅማችንን አጎልብቶታል--- መምህራን

67

ግንቦት 8 ቀን 2011በመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲው የተሰጣቸው ተግባራዊ የሙያ ስልጠና ቀደም ሲል የነበረባቸውን የአቅም ክፍተት ለመሙላት እንዳስቻላቸው ከባሌና ምዕራብ አርሲ ዞን የተውጣጡ መምህራን ገለጹ። 

ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ በተለያዩ ጊዜያት የጥናትና ምርምር ውጤትን መሰረት በማድረግ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተገበረ መሆኑን አስታውቋል። 

ስልጠናውን የተከታተሉ መምህራን በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዜያት የሚሰጣቸው ሙያዊ የሥራ ላይ ስልጠናዎች ታግዘው አቅማቸውን እያሻሻሉ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ከባሌ ዞን ዲንሾ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣው መምህር ሽቱ ንጋቱ እንደገለጸው ከዚህ በፊት በሚያስተምርበት የትምህርት መስክ ለተማሪዎቹ ሳቢና ቀላል በሆነ መንገድ የትምህርቱን ጭብጥ ለማስተላለፍ ይቸገር እንደነበር አስታውሷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ምሁራን በተሰጠው ሙያዊ ስልጠና በማስተማር ዘዴዎች፣ በግምገማ ሂደትና አይነቶች ላይ ተጨማሪ ዘመናዊ እውቀት ማግኘቱን አስረድቷል፡፡

ስልጠናው በቀጣይ በንባብ ራስን በማብቃት ተወዳዳሪ ሙያተኛ ለመሆን መነሳሳት እንደፈጠረበትም ነው የገለጸው፡፡

“ተምረን የዘናጋናቸውን የተለያዩ ዓይነት የማስተማሪያና የመገምገምያ ስልቶች እንድናስታውስ ስልጠናው ረድቶናል” ያለችው ደግሞ ከምዕራብ አርሲ የመጣችው መምህርት መሰረት ሙሉጌታ ናት፡፡ 

እንደ መምህርቷ ገለጻ በዩኒቨርሲቲው የተሰጣቸው ስልጠና አቅማቸውን ለማጎልበት ከሚያደርገው እገዛ በተጨማሪ ለትምህርት ጥራት መጎልበት ጉልህ ጠቀሜታ አለው። 

በዩኒቨርሲቲው የዴሊቬሮሎጂ ዩኒት ዲን ዶክተር በዛብህ ወንድሙ በበኩላቸው እንደገለጹት ስልጠናው የሁለተኛና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ መምህራን በትምህርት አሰጣጥና በግምገማ ጥራት ላይ የሚስተዋሉባቸውን ችግሮች ለማቃለልና ጊዜው ከሚጠይቀው እውቀት ጋር እራሳቸውን እንዲያበቁ ለማስቻል ያለመ ነው።

“የዩኒቨርሲቲው መምህራን በተለያዩ ጊዜያት በታችኛው እርከን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመማር ማስተማር ሥራ ላይ ያካሄዷቸው ጥናቶች መምህራን በሚያስተምሩት የትምህርት መስክ ላይ በቂ እውቀት ቢኖራቸውም እውቀቱን በማስተላለፍ ላይ ተግዳሮቶች እንደሚታዩባቸው አመልክተዋል” ብለዋል፡፡ 

እንደ ዶክተር በዛብህ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ መተግበሩንና በእዚህም ችግሮችን ለማቃለል በትኩረት እየሰራ ነው። 

በባሌና ምዕራብ አርሲ ዞኖች በሚገኙ የሁለተኛና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚያስተምሩ መምህራን የተሰጠው ተግባር ተኮር ሙያዊ ስልጠናም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን አመልክቷል፡፡

ስልጠናው የትምህርት ጥራት እንዲጠበቅ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸው በየደረጃው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን በትምህርት አሰጣጥ ስልቶችና በተለያዩ የምዘና ስርአቶች ላይ ወጥ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ በኩልም ስልጠናው አጋዝ መሆኑን አስረድተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ተወካይ ዶክተር ሀሰን ሺፋ በበኩላቸው ተቋሙ በተለያዩ ዘርፎች የኅብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ የትኩረት መስኮች ላይ ያተኮሩና 50 የሚደርሱ የማህበረሰብ አገልግሎት የምርምርና ጥናት ሥራዎችን በማከናወን ላይ መሆን አስረድተዋል፡፡ 

እንደተወካዩ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት 300 የሚጠጉ ምርምሮችና የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮጀክቶችን አካሂዷል።

በ1997 ዓ.ም የተቋቋመው የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት 20ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ጠቅሶ የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም