በቅዱስ ያሬድ እና ግእዝ ቋንቋ ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ በአክሱም እየተካሄደ ነው

128

አክሱም ግንቦት  8/2011 ሶስተኛው የቅዱስ ያሬድ እና ግእዝ ቋንቋ ኮንፈረንስ በአክሱም ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ ነው።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጸሐዬ አስመላሽ በኮንፍረንሱ መክፈቻ ስነስርዓት ወቅት እንዳሉት ተቋሙ የአክሱም ከተማ የያዘችው የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ለማልማት እና ለማስተዋወቅ እየሰራ ነው።

"ለሶስተኛ ጊዜ አለም አቀፍ ኮንፈረንስ ሲያዘጋጅ 1ሺህ 500 ዓመታት ያስቆጠሩት የቅዱስ ያሬድ ስራዎችን ለአለም ለማስተዋወቅ ነው"ብለዋል።

የቅዱስ ያሬድ ስራዎች በተለይ በሳይነሳዊ መንገድ እንዲጠና እና መረጃዎቹ በሰነድ እንዲደራጁ ዩኒቨርሲቲው የጀመራቸው ስራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

በየዓመቱ የሚካሄደው ኮንፈረንሱ የቅዱስ ያሬድ ስራዎች በማስተዋወቅ የቱሪዝም ልማት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ፣ፍልስፍና ፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እና ተመራማሪ ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም "ቅዱስ ያሬድና ፍልስፍና " በሚል ጥናታዊ ፅሑፍ አቅርበዋል።

በጹሑፋቸው እንዳመለከቱት ቅዱስ ያሬድ ስለ ተፈጥሮና ፍልስፍና የነበረው እውቀት የላቀ ፣ የራሱ ዜማዎች እና የሙዚቃ ኖቶች ቀድሞ የፈጠረ ሊቅ ነው።

ስራዎቹ ለቤተክርስቲያን እና ለአለም ያበረከተው አስተዋጽኦ በሰነድ ተዘጋጅቶ ለትውልድ ለማስተላለፍ የሚመለከታቸው አካላት ሊሰሩበት እንደሚገባ አመላክቷል።

"ቅዱስ ያሬድ የሰው የትውልድ ሂደትና ፍልስፍና ያሳየ ሊቅ ነው"ያሉት ምሁሩ ነገሮች ከተፈጥሮ ጋር አዛምዶ የመፃፍ ችሎታ እንደነበረው ገልጸዋል።

"የቅዱስ ያሬድና ግእዝ ቋንቋ አበርክቶ "በሚል ርዕስ ጽሁፍ ያቀረቡት የታሪክ ምሁርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር አድሃና ኃይሌ በበኩላቸው የግእዝ ቋንቋ እስከ 1847 ዓ.ም የክርስትና ኃይማኖት እና የመንግስት የስራ ቋንቋ እንደነበረ አስታውሰዋል።

ጽሁፉን ያቀረቡትም የሊቁ ስራዎችና ግእዝ ለሀገሪቱ ትልቅ የቱሪዝም ሃብቶች በመሆናቸው ጥቅም ላይ ለማዋል ሊሰራበት እንደሚገባ ለማመልከት እንደሆነ  ተናግረዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፍረንስ በቅዱስ ያሬድ ስራዎችና ግእዝ ቋንቋ ላይ ያተኮሩ ስድስት ጥናታዊ ፅሑፎች እንደሚቀርቡ ታውቋል።

ከተለያዩ የሀገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተወጣጡ ምሁራንና ተመራማሪዎች በኮንፍረንሱ እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም