ለፋብሪካዎች የሚደረገው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ፍትሃዊነት ይጎድለዋል – አማራ ክልል

155

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2011 በአማራ ክልል ለሚገኙ ፋብሪካዎች የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ፍትሃዊነት እንደሚጎድለው የክልሉ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው ምላሽ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም ቢኖርም፤ የፍትሃዊነት ችግር እንዳይከሰት እያከናወነ ያለው ተግባር ጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን ገልጿል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መጋቢያው ጣሰው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትእንደገለጹት፤ በክልሉ ያለው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጥያቄ በስራ ላይ ላሉት ፋብሪካዎች ብቻ አይደለም፣ ለአዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማቋቋም ቢሆንም በፍትሃዊ መንገድ ለማግኘት ችግር አጓጥማል።

አዳዲስ ፋብሪካዎችን ለማስጀመርና የጥሬ ዕቃ ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳጋጠመ ገልጸዋል።

“ፋብሪካዎች ቁመህ ጠብቀኝ ባለመሆናቸው ስጋታችን እያደገ መጥቷል” ያሉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር፤ አዳዲስ ፋብሪካዎች ከተቋቋሙ በኋላ ማምረቻ መሳሪያዎችን ግዥ ተፈጽመው የውጪ ምንዛሪ በወቅቱ ማግኘት ሳይቻል በመቅረቱ በደንበኞች ዘንድ እምነት ማጣት መከሰቱን አመልክተዋል።

ይህም ግዥ ከፈጸምን በኋላ በጊዜ ልዩነት የዋጋ ልዩነቱ አለመስማማትና እምነት ማጣት ችግሮች በደንበኞቻቸው ላይ እያጋጠማቸው መሆኑን ገልጸው፤ ‘አሁን ላይ በአራት ደንበኞች ላይ ይህ ችግር አጋጥሞናል’ ነው ያሉት።

በቅርቡ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መለዋወጫ እቃዎች ማስገባት ያልቻለ አንድ ድርጅት ስራ ማቆሙንም ለአብነት አንስተዋል።

ባለስልጣኑ ችግሩን ለብሔራዊ ባንክ በተደጋጋሚ መጠየቁን አውስተው፤ ‘ቢዘገይም በቅርቡ ምላሽ የሰጡባቸው አሉ፣ ምላሽ ያላገኘንባቸው ጥያቄዎችም አሉ’ ብለዋል።

በዚህ ምክንያት “በብዙ ትግል ያፈራናቸውን ባለሙያዎች እያጣን ነው፤ የግል ድርጅቶችም ሆኑ የመንግስትና የግል ጥምር ኩባንያዎች ስራቸውን ያቆማሉ የሚል ስጋት እንዳረባቸው አብራርተዋል። 

ጥያቄው የድርጅቶች የመኖርና አለመኖር ጉዳይ መሆኑን አመልክተው፤ ባንኩ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት እንዳለበት ነው የገለጹት።

እንደዋና ዳይሬከተሩ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት የውስጥም ሆነ የውጭ ግል ዘርፍ በሽርክና ገብቶ ኢንቨስት ለማድረግ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ተግዳሮት ሆኗል።

በክልሉ ለኤሌትሪክ ሃይልና ተያያዥ ችግሮች አካባቢያዊ መፍትሄ የመስጠት ዕድል መኖሩን ገልጸው፤ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ፍትሃዊ የማድረግ ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጠውታል።

በብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ክትትል ስራ አስኪያጅ አቶ መሃሪ መንግስቱ በተነሳው ጉዳይ ላይ በሰጡት ምላሽ እንደገለጹት፤ አገሪቷ ከወጪ ምርቶች ሽያጭ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መጥቷል።

ባንኩ ከስንዴና ማዳበሪያ ግዥዎች ጨምሮ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚለቅ አውስተው፤ ባንኩ “የውጭ ምንዛሬ አቅረቦቱ ፍትሃዊነት ይጎድለዋል” ለተባለው ጉዳይ ግን ባንኩ በተቻለ መጠን ፍትሃዊነት ችግር እንዳይከሰት ያከናወናቸው ተግባራት በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ አብራርተዋል።

በቅርቡም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ከ300 ሚሊየን ዶላር፣ ለግል ባንኮች ደግሞ ከ100 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ በመሰጠት ለማኑፋክቸሪንግና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ምርቶች ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።

ከፍላጎቱ አኳያ የውጭ ምንዛሬ ማቅረብ ባይቻልም ብሔራዊ ባንክ ለሌሎች ባንኮች “ሃላፊነት ተሰጥቶ ስርጭቱን እየተቆጣጠረ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ቅደሚያ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በቅርቡ ለአዜአ እንዳስታወቁት፤ በተለያዩ ምክንያቶች አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ያህል የውጭ ምንዛሬ ማቅረብ አልተቻለም። ነገርግን ኢኮኖሚውን አሁን ባለበት ሁኔታ ማስቀጠል የሚያስችል በቂ የውጭ ምንዛሬም አለ።


ባለፉት ዓመታት የተቀዛቀዘውን የወጪ ንግድ ማሳደግ ግን ዋነኛው የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት የሚያስችል በመሆኑ በተለይ በግብርናው ዘርፍ ላይ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።