የማዕድን ሃብትን በአግባቡና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ያስችላል የተባለው አዋጅ ጸደቀ

331

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2011 ኢትዮጰያ ያላትን የማዕድን ሃብት በአግባቡና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚስችላትን አዋጅ አሻሻለች።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በካሄደው የ4ኛ ዓመት 39ኛ  መደበኛ ስብሰባው የተፈጥሮ ሃብት መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያቀረበለትን የማዕድን ግብይት አዋጅ መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባል ወይዘሮ ጀምበርነሽ ክንፉ ረቂቁን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የተሻሻለው አዋጅ አገሪቷ ያላትን ሃብት በአግባቡ እንድትጠቀምና ህገ-ወጥ የማዕድናት ዝውውር ለመግታት የሚያስችል ነው።

አዋጁ ለወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል ለመፍጠርና የግብይት፣ የፈቃድና የምስክር ወረቀት ስልጣንን ለይቶ በአግባቡ ያስቀመጠ መሆኑን ጠቁመዋል።

በነባሩ አዋጅ የከበሩ ማዕድናት የላኪነት የብቃት ማረጋጋጫ የወሰደ ሰው ያለገደብ ሁሉንም አይነት የከበሩ ማዕድናት ወደ ውጭ የመላክ ስልጣን ያለው ሲሆን ይህም ለሌሎች ዜጎች የስራ ዕድል የማይከፍት ነበር።

በተሻሻለው አዋጅ ግን የሚሰጠው ፈቃድና ብቃት በማዕድን ዓይነት ተለይቶ እንዲሰጥ ያደርጋል፤ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥር ተደርጎ የተዘጋጀም ነው ብለዋል።

በአዋጁ ህገወጥ የማዕድናት ዝውውርና ግብይት ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎች ተግባሩ ከሚያስከትለው ጉዳት ጋር የሚመጣጠንና አስተማሪ የሆነ ቅጣት አስቀምጧል።

በተጨማሪም ማዕድናት በሚገኝባቸው አካባቢዎች የበለጠ በማዕድናት ላይ  እሴት ለመጨመርና  የማዕድናት ህገ-ወጥነትን ለመከላከል እንደ አስፈላጊነቱ የማዕድናት የገበያ ማዕከል ለመቋቋምም አዋጁ ፈቅዷል ።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።

 የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ረቂቅ አዋጅንም ለሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መምራቱ ታውቋል።

ምክር ቤቱ በዛሬ ውሎው የኢትዮጰያ ፕሬስ ድርጅትን እንደገና ለማቋቋም የቀረበውን ረቂቅ አዋጅንም መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ለህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  መርቷል።