በይገዙ ዳባ የክስ መዝገብ ስር የከባድ ሙስና ወንጀልተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን አቀረቡ

135

ግንቦት 7 /2011 በአቶ ይገዙ ዳባ የክስ መዝገብ ስር በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው 10 ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ላይ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል።

ተካሳሾቹ ከ2010  እስከ 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ  መንግስት  ለገበያ  ማረጋጊያ  በፈጸመው ዓለም  አቀፍ  የስንዴ  ግዥ ስምምነት የማይገባ ጥቅም  ለማግኘት  በማሰብ  ህዝብና መንግስት የሚጎዳ ድርጊት ፈጽመዋል በሚል ነው የተከሰሱት።

ተከሳሾቹ 'ፕሮሚሲንግ  ኢንተርናሽናል' ለተባለ ተቋም ጥቅም ለማስገኘት ወይም በመንግስት ጥቅም ላይ ጉዳት ለማድረስ በማሰብ በተሰጣቸው ሃላፊነት መሰረት ሊጠብቁትና ሊከላከሉት የሚገባቸውን በመተላለፍ የመንግስትን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ፈጽመዋል ሲል ነው ዐቃቤ ህግ ክስ የመሰረተባቸው።

”በዚህም በመንግስት ላይ 24 ሚሊዮን ዶላር ወይም 600 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ጉዳት አድርሰዋል ይላል” ክሱ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት አንደኛ ወንጀል ችሎት ከሁለት ሳምንት በፊት ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ ላይ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያቸውን እንዲያቀርቡ ለግንቦት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ከትላንት በቀጠለው የዛሬው ችሎት ውሎም አንደኛ ተካሳሽ አቶ ይገዙ ዳባ እና አስረኛ ተካሳሽ ጆንሴ ደገፋ በጠበቆቻቸው በኩል የክስ መቃወሚያቸውን አቅርበዋል።

አቶ ይገዙ ዳባ በክስ መቃወሚያቸው አንድ ካምፓኒ ከህጉና ውሉ ውጭ ምን አይነት ልዩ ድጋፍ ማድረግ እንደነበረብኝ ያልተገለጸ በመሆኑ፣ የጥፋተኛነት ውሳኔ እንዲሰጥበት ለኤጀንሲው አዘግይቶ አቅርቧል ያለውም ለምን ያህል ጊዜ እንዳዘገየሁና መቼ ማቅረብ እንደነበረብኝ ያልተገለጸና ያልተብራራ በመሆኑ ከመመሪያ አሰራር ውጭ ፈጽሟል የተባለውም የትኛውን አሰራር እንደተላልፍኩ አልተገለጸም ብለዋል።

በመሆኑም ክሱን ለመከላከል የማያስችለኝ ስለሆነ ዐቃቤ ህግ ክሱን አብራርቶና አሻሽሎ እንዲያቀርብ እንዲታዘዘልኝ ሲሉም ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ሀተታ በጥቅሉ ሲታይም የጨረታ መሰረዝና እንደ ውሉ አለመፈጸም የሚል መሆኑንና ይህ የውል ማስተዳደርና የመፈጸም ድርጊት በፍትሐ ብሔር ወይም በአስተዳደር ደንብ መሰረት የሚታይ ከመሆኑ በቀር በወንጀል አያስከስስም ተብሎ ከክሱ ነጻ እንዲያሰናብተኝ ሲሉም በክስ መቃወሚያቸው አቅርበዋል።

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ክሱ ያስረዳልኛል በማለት ያቀረባቸው 43 የተለያዩ የጽሁፍ ማስረጃዎች በየትኛው ማስረጃ በየትኛው ተከሳሽ ላይ እንደሚያስረዳ የማይገልጽ ከመሆኑም በላይ በደፈናው በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን ይህ አቀራረብ ክሱን ለመከላከል የማያስችል መሆኑንና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ችሎት በመዝገብ ቁጥር 73514 ከሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ ውጭ ስለሆነ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ያቀረበውን የሰነድ ማስረጃ ለይቶ እንዲያቀርብ ሲሉም አቶ ይገዙ ዳባ ጠይቀዋል።

አቶ ይገዙ ጨምረውም ዐቃቤ ህግ ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓ.ም ባቀረበው ክስ የፖለቲካ ሹመኛ የሆንኩትን 1ኛ ተከሳሽ እና በሙያ የስራ ሃላፊነት የቀረበባቸውን ሌሎች ተከሳሾች ጋር በማጠመር ክስ እንዳቀረበባቸውና በድርጊቱ የሚያስጠይቅ ነው ከተባለ እኔ ልጠየቅ የሚገባው የስራ ሃላፊነቴን በቸልተኝነት ባለመወጣት በሚደነግገው የወንጀል ህግ ስር በመሆኑ ዐቃቤ ህግ ክሱን አሻሽሎና ነጥሎ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ይስጥልኝ ብለዋል በክስ መቃወሚያቸው።

10ኛ ተከሳሽ አቶ ጆንሴ ደገፋ በበኩላቸው ዐቃቤ ህግ ያቀረባቸው የጽሁፍ ማስረጃዎች የትኛውን ድርጊት እና የትኞችን ተካሳሾች እንደሚመለከቱ ለያይቶ እንዳልገለጸ በክስ መቃወሚያቸው አቅርበዋል።

በጽሁፍ ማስረጃዎቹ ውስጥ አንዳንዶቹ የቀረቡት በእንግሊዘኛ ቋንቋ በመሆኑ በአማርኛ ቋንቋ እንዲያስተረጉም እንዲታዘዝም ጠይቀዋል።

በአጠቃላይ ዐቃቤ ህግ በተከሳሹ ላይ ባቀረበው ክስ የክርክሩ መቀጠል የተከሳሽን መብት የሚያጠብና የክስ ማመልከቻውም ተካሳሽን ያሳሳተና የሚያሳሰት ስለሆነ ዐቃቤ ህግ ክሱን ለውጦና አሻሻሎ እንዲያቀርብ እንዲታዘዝም አመልክተዋል።

ከ2ኛ እስከ 9ኛ ያሉ ተከሳሾች በትናንትናው የችሎት ውሎ የክስ መቃወሚያቸውን ማቅረባቸው የሚታወስ ነው።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት አንደኛ ወንጀል ችሎት ፌዴራል ዐቃቤ ህግ በተካሳሾች የክስ መቃወሚያ ላይ በሚሰጠው አስተያየትና ተካሳሾች ባቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 6 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም