በምርጫ 97 በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎችን አጣርቶ የያዘው ሪፖርት በእርቀ ሰላም ኮሚሽን ሊታይ ነው

115

አዲስ አበባ ግንቦት 7/2011ከምርጫ 1997 በኋላ የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎችንና የደረሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት የያዘ ሪፖርት የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እንዲያየው ተላለፈ።

በወቅቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትከፖሊስ የደረሰውን ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ ሁከቱን ለማስቆም በመንግስት የተወሰደውን እርምጃ በሚመለከት የሚያጣራ ኮሚሽን ማቋቋሙ ይታወሳል።

እርምጃውተመጣጣኝ መሆን አለመሆኑን፣ ከሁከቱ ጋር በተያያዘ የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የጠፋ የሰው ህይወትና የንብረቶችን እንዲያጣራ 11 አባላት ያሉት ኮሚሽንም በምክር ቤቱ ተቋቁሞ ነበር።

ኮሚሽኑ በወቅቱ መንግስት የወሰደውን እርምጃ በተመለከተ "ተመጣጣኝ አለመሆኑንና የሰብአዊመብት ጥሰት መኖሩን የሚያሳይ ሪፖርት በማቅረቡ ከመንግስት አካላት በደረሰበት ማስፈራሪያ የኮሚሽኑ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ ላለፉት 13 አመታት በስደት ላይ ቆይተዋል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ አቶ ፍሬህይወት ሳሙኤልካለፈው አንድ አመት ጀምሮ በተለያየ ምክንያት ከአገራቸው የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ሰብሳቢው ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት አጣሪ ኮሚሽኑ በወቅቱ የተወሰደውን እርምጃ ለማጣራት ለሰባት ወራት ምርመራ በማድረግ የውሳኔ ሃሳብ ማዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በተደረገውማጣራትም 193 ሲቪሎችና 6 ፖሊሶች መሞታቸውን፣ 763 ሲቪሎች መቁሰላቸውን፣ 65 ፖሊሶች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውና 50 ሺህ ሰዎች መታሰራቸውን ጠቅሶ "መንግስት የወሰደው እርምጃ ከመጠን ያለፈ" መሆኑን ሪፖርት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በወቅቱ በቀረበው ሪፖርት "ውሳኔ ለማስቀየር ጫና እንደተደረገባቸው" የተናገሩት ሰብሳቢው ሃሳባቸውን ባለመቀየራቸው ከመንግስት አካላትየደረሰባቸው ተጽእኖ ለህይወታቸው አስጊ በመሆኑ ከአገር መውጣታቸውን ገልጸዋል።

እሳቸውም ሆነ የስራ ባልደረቦቻቸው በደረሰባቸው ቂምና በቀልን ይዘው ሳይሆን ለእርቅና ለሰላም እንደመጡ ተናግረው በእጃቸው የሚገኘው የምርመራ ውጤት በእርቀ ሰላም ኮሚሽን እንዲታይ ተስማምተዋል።

እንደ አቶ ፍሬህይወት ገለፃ "በወቅቱ በምርጫ ቦርድ፣ በፍትህ ተቋማት፣ በፖሊስና ሌሎች ተቋማት" ገለልተኛ እንዳልነበሩ ያምናሉ።

የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የትነበርሽ ንጉሴ በእርቀ ሰላም ሂደቱ አቶ ፍሬህይወት እገዛ እንዲያደርጉ ጠይቀዋቸዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት ሰላምና ፍቅር አጀንዳ ሆኖ ጎልቶእንዲወጣ  ቂም፣ ቁርሾን ትቶ በአንድነት አገርን ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።

በምርጫ 1997ን ተከትሎ የተፈጸሙ በደሎች የሰላምና እርቅ ኣካል እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዚህም ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስረከብ መንግስት የቻለውን ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።

አፈ ጉባኤው "በመካከላችን ያለውን ጥላቻ አስወግደን በሰላም በፍቅር ኢትዮጵያን በማሳደግ ለቀጣዩ ትውልድ በጎ ተግባርን እናውርስ" በማለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም