በቦርድ አባላት አለመሟላት በወቅቱ ሊሰሩ የሚገቡ ተግባራትን ማከናወን አልቻልኩም--ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ

132

ግንቦት 7/2011 በቦርድ አባላት አለመሟላት በወቅቱ ሊሰሩ የሚገቡ ተግባራትን ማከናወን አልቻልኩም ሲል ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታወቀ

በቦርዱ ሊከናወኑ ከሚገቡ ተግባራት ብዙዎቹ መጓተቱ ይወሳል። ለአብነትም የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ከአምስት ወራት በፊት ቢቀረብም ከቦርድ አባላት አለመሾም ጋር ተያይዞ ቦርዱ በሪፈረንደም ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት እንዳልቻለ ነው የተገለጸው።

ቦርዱ ይህን ይፋ ያደረገው የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጽሙን በተወካዮች ምክር ቤት ለሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ ባቀረበበት ወቅት ነው።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት ተቋሙ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በህዝብ ዘንድ ያለበትን እምነት ማጣት ለመመለስ በተቋማዊ አደረጃጀትና ህግ ማሻሻያ የሪፎርም ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

የፓርቲዎች የጋራ ውይይቶች፣ የቃል ኪዳን ሰነድ ዝግጅትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ስትራቴጂዎችን የመንደፍ ስራዎችን እንደ አብነት ያነሱት ሰብሳቢዋ፤ ምርጫን ነጻ፣ ገለልተኛ ታማኝነት ያለው ለማድረግ ተቋማዊ የለውጥ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከቋሚ ኮሚቴ አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡባቸው ጥያቄዎች መካከል የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን ሪፈረንደም ለማካሄድ ቦርዱ ለምን ዘገዬ የሚለው ይገኝበታል።

የሲዳማ የክልልነት ጥያቄም  ከአምስት ወራት በፊትና ሃላፊነት በተረከቡ በሳምንታት ውሰጥ መቅረቡን ሰብሳቢዋ አስታውሰዋል።

ምርጫ ቦርድ ሪፎርም ሁሉ አቀፍ መሆኑንና የፖለቲካው ሁኔታ ተለዋዋጭነት እንዳለው ጠቅሰው፤ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔም ከሌሎች የምርጫ ቦርድ ቁልፍ ስራዎች ተለይቶ በቀላሉ የሚፈታ አለመሆኑን ነው የተናገሩት።

ህዝበ ውሳኔ የሚደረገው ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ሳይሆን ግልጽና ትክክለኛነት ባለው የህዝበ ውሳኔ አካሄድ መሆኑን ገልጸው፤ የሲዳማ ጥያቄም አስፈጻሚዎችን መርጦ ስራውን ለማከናወን ሰፊ ስራ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።

በውጭ የነበሩም ሆነ በአገር ውስጥ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ ሂደት በተመለከተም በቦርዱ ህጋዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን አሟልተው የተመዘገቡ 16 ብቻ ሲሆኑ በከፊል ሳያሟሉ ከተመዘገቡት ጋር ደግሞ 66 መሆናቸው ተገልጿል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባን የሚመከለት የህግ ማዕቀፍ እየተሻሻለ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ አገራዊ ለውጡን መሬት ለማስነካት ሲባል ያልተመዘገቡ የፓለቲካ ድርጅቶች የአደረጃጀት ሂደታቸውን እንዲሰሩ የትብብር ስራዎች እየተደረገላቸው መሆኑን አንስተዋል።

በተሻሻለው የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረትም ቦርዱን ከሚመሩ 9 አባላት ቁጥር ወደ አምስት እንዲቀነሱ ቢደነገግም አባላቱ በምክር ቤቱ ተሹመው ወደ ስራ አልገቡም ብለዋል።

ይህ ደግሞ ቦርዱ የሲዳማን ህዝበ ውሳኔም ሆነ ሌሎች ተግባራቱን ማከናወን ያለበትን ስራዎችና የሚቀርቡ ጥያቄዎቸን በፍጥነት ለማከናወን ችግር እንደፈጠረበት አስረድተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመን መዝጊያ ጊዜ በመቃረቡም የአባላቱ ሹመትና የህግ ማዕቀፎች በፍጥነት ጸድቀው ወደ ስራ መገባት እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የቦርዱ የዘጠኝ ወራት አፈጻፀም 71 በመቶ ሆኖ ይህንን ዝቅተኛ አፈጻጸሙን በቀሪ ወራት ዕቅዱን በማከናወን እንዲያሻሸል  አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም